Search

ቀይ ባሕርን የሞት ሽረት ህልውናቸው አድርገው ያገለገሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባላት

ሰኞ ኅዳር 01, 2018 248

የኢትዮጵያን ልዕለ ኃያልነት የሚፈሩ ኃይሎች በሴራ የባሕር በሯን እንድታጣ ማድረጋቸውን የሚናገሩት የቀድሞው ባሕር ኃይል መኮንን ሌፍተናንት ፈረደ አየለ፤ እነዚህ አካላት ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት ከሀገር ውስጥም ከውጭም ያሉ ባንዳ እና ባዳዎችን ተጠቅመዋል ይላሉ።
ይህም ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተቀባይነት በማሳጣት ሉዓላዊነቷን የመጣስ፣ በኢኮኖሚ አቅሟ ደካማ ሆና እንድትቆይ የማድረግ ቀደም ብሎ የተጀመረ የሴራ ፖለቲካ ውጤት መሆኑንም ሌፍተናንት ፈረደ አየለ ይናገራሉ።
 
ከ30 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ልታጣ በተቃረበችበት፣ የባሕር ኃይሏ ሊበተን ከጫፍ በደረሰበት ወቅት የቀድሞው የባሕር ኃይል አመራር ብርጋዴር ጄነራል ተሰማ ተሾመ በንዴት ራሳቸውን መሰዋታቸውን ልጃቸው በእምነት ተሾመ ትናገራለች።
በእምነት አባቷ በውትድርና መስክ ተሰማርተው ሀገራቸውን እና ወገናቸውን ባገለገሉበት ወቅት ቀይ ባሕርን የሞት ሽረት ጉዳያቸው አድርገው ይመለከቱት እንደነበር ትገልጻለች።
 
በሴራ የፈረሰው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በጊዜያዊነት ይፍረስ እንጂ መቼም ቢሆን ከኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ አይጠፋም ብለው የሚያምኑት ብርጋዴር ጄነራል ተሾመ ተሰማ፤ ከመሰዋታቸው በፊት ኢትዮጵያውያን የባሕር በራቸውን እንዲያስከብሩ የአደራ መልዕክት ትተው ማለፋቸውን ልጃቸው በእምነት ተናግራለች።
የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሲሉ አባቷን ጨምሮ በርካታ የባሕር ኃይል ወታደሮች የተሰውት ቀይ ባሕር ከደም እና ከአጥንታቸው ጋር የተዋሃደ ስለነበር ነው የምትለው በእምነት፤ የባሕር በር አሁን ጥያቄ ሆኖ በትውልዱ በመነሳቱ ደስታ እንደተሰማት ከኢቲቪ ጋር በነበራት ቆይታ ገልጻለች።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ተዘግቶባት ለዘለዓለም መቆየት እንደማትችል የሚገልጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሀገሪቱ በቀይ ባሕር ላይ መልክዓ ምድራዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መብት እንዳላት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲያስገነዝቡ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ከ3 አስርት ዓመታት በፊት ሰፊ የባሕር ክልልን በባለቤትነት የያዘች፣ በተደራጀ የባሕር ኃይሏ ከራሷ አልፎ የቀጣናውን ደህንነት የምትጠብቅ እንዲሁም በወደቦቿ ንግድን የምታሳልጥ የቀጣናው ኃያል ነበረች።
የአሁኑ ትውልድ የባሕር በር የመብት ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት እና ለኢኮኖሚ ዕድገቷ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።
በመሐመድ ፊጣሞ