Search

ልትጠፋ የነበርችን ሀገር ታድጎ በጠንካራ መሰረት ላይ የገነባው የቱርካውያኑ መሪ

ማክሰኞ ኅዳር 02, 2018 1978

ብዙዎች ሙስጠፋ ከማል ከሚለው ስም ይልቅ 'የቱርክ አባት' ወይም 'አታቱርክ' በሚለው ስሙ ያውቁታል። በዘመናዊቷ ተርኪዬ የዚህን ሰው ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና  የእርሱ ዐሻራ የማይገኝበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል።

በቱርካውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለውንና እስከዛሬም ድረስ  ፎቶው ከአብዛኛዎቹ ቱርካውያን መኖሪያ ቤት ውስጥና በየቢሮው ግድግዳ ላይ የሚታየው ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት ቱርክ በኦቶማን ግዛት ሥር ነበረች።

በኦቶማን ቱርክ የተስፋፋ የግዛት ዘመን እስከ ደቡብ ምስራቅ አውሮፓ እና መካከልኛው ምስራቅ ደርሶ ቬና እና የአሁኗን ሃንጋሪን አካሎ በባልካን ቀጣና ግሪክ እና የዛሬዋ ዩክሬንን ጨምሮ በኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ግብጽ እና ሰሜን አፍሪካ ድረስ የሚቆጣጠራቸው ቦታዎች ነበሩት።

እንዲህ በግዛት መስፋፋት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የስልጣኔ ማማ ላይ የነበረው የኦቶማን ኤምፓየር በመላው ዓለም ሊስፋፍ የሚችል አቅም እንዳለው በወቅቱ መገመት ስህተት አይሆንም።

ይሁን እንጂ የአንደኛው የዓለም ጦርነት መጀመር ለኦቶማን ኤምፓየር ስጋትም ዕድልም ይዞ የመጣ ይመስል ነበር። በወቅቱም ገለልተኛ ሆኖ መቆየትን ሲከተል የነበረው የኦቶማን ኤምፓየር የጀርመን ግስጋሴ ግን እድል ይዞ እንደሚመጣ ያሰቡት የወቅቱ የኤምፓየሩ መሪዎች ገለልተኝነቱን ትተው ወደጦርነቱ መግባትን መረጡ።

የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ ግን ለኦቶማን ቱርክ ዝም ብሎ ማብቃት ብቻ አልነበረም። ይልቁንም የወቅቱን ሰፊ ግዛት አጥፍቶ ቱርክ የምትባል ሀገርን ሊያጠፋ ጫፍ የደረሰ ጦርነት በየአቅጣጫው ወረራት። በሀገር ቤትም በተለያዩ ፍላጎቶች ውስጥ የነበሩ ቡድኖች የተነሳውን ጦርነት በየአቅጣጫው እያነደዱ ያንን ታላቅ ሀገር ለማጥፋት እሳት ጫሪ ሆነው ብቅ ብቅ አሉ።

የ600 ዓመታት እድሜ ያስቆጠረው የኦቶማን ቱርክ ኢምፓየር በአንደኛው የዓለም ጦርነት መሸነፉን ተከትሎ እንደ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ግሪክ እና ሌሎች አሸናፊ ኃይሎች የቱርክን መሬት ለመቀራመት እና በወረራ ለመያዝ ጦርነት የጀመሩበት ዘመን ነበር።

ይሄኔ ታዲያ የኦቶማን ኤምፓየር የዛሬዋን ቱርክን ይዞ ሊጠፋ ከጫፍ እንደደረሰ የተመለከተው አርበኛ ሁሉንም ቦታ  ለማስያዝ ቆርጦ ሲነሳ ማንም ይሳካለታል ብሎ የገመተ አልነበረም።

የመከፋፈል እና መነታረክ ውጤት የሆነ ጦርነት ሲነድባት ለነበረች ሀገር፣ የጋራ መታረቂያ ታሪክ አበጅቶ የመስማሚያ መንገዱን አሳይቶ አዲስ እና ዘመናዊት ቱርክን ፈጥሮ ለትውልድ ያስተላለፈው ሰው በእርግጥም በተዓመር ካልሆነ በስተቀር እንዴት ይሳካል የሚያስብል ሥራ መስራቱን ዛሬ ቱርካውያን ሁሉ በኩራት ይመሰክሩለታል።    

ሙስጠፋ ከማል የቱርክ አዳኝ (ታዳጊ) ሆኖ ወደ ስልጣን የመጣው  የንጉሣዊው መንግሥት አስተዳደር ደክሞ ቱርክ በሌሎች ሀገራት ቅኝ አገዛዝ ስር ለመውደቅ በተቃረበችበት ወቅት ነበር።

በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎቻቸው ውስጥ የህን ሰው አለማስታወስ አይችሉም። አገልግሎት ላይ ባሉ ከአምስት  እስከ ሁለት መቶ ሊሬ የቱርክ የመገበያያ ኖቶች ላይ እንዲሁም በሳንቲሞቻቸው ላይ ገዝፎ የሚታየው የዚህ ሰው ምስል ነው።

በቱርክ ውስጥ  በሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ስም የተሰየሙ የመታሰቢያ ቦታዎች እና ተቋማት ብዛት ለቁጥር ያዳግታል። በአብዛኛው የቱርክ ከተሞች  ሐውልቶች ተቀርፀውለታል አደባባዮችና መንገዶች በስሙ ይጠራሉ።

በዋና ከተማይቱ ኢስታንቡል የሚገኘው ትልቁ የተርክዬ የአየር ማረፊያ፣ ግዙፉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ፣ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ቤቶች፣  ሙዚየሞችና ስታዲየሞች በከማል አታቱርክ ስም ተሰይመዋል።

በኦቶማን ጦር ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የጦር መኮንን የነበረው ከማል አታቱርክ በጋሊፖሊ ጦርነት በሀገሩ ላይ የተቃጣውን ጥቃት  በመመከት ወታደራዊ ድልን ተጎናጽፏል። ከዚያም በኋላ የንጉሣዊ ሥርዓት (ሱልጣኔት) መዳከም ተገንዝቦ ሀገሩን ሊወሩ ባሰፈሰፉ ወራሪ ኃይሎች ላይ  የተቀዳጀው ድል በህዝቡና በጦር ኃይሉ ዘንድ አመኔታ እንዲያገኝ አስችሎታል።  እናም ተዳክሞ በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ስር የወደቀውን የአፄ ሥርዓት ለማስወገድ ሲነሳ በህዝቡ ዘንድ ድጋፍ ለማግኘት አስችሎታል።

ከማል አታቱርክ በዚህ አይነት መልኩ ንጉሣዊውን ሥርዓት (ሱልጣኔትን) ካስወገደ በኋላ  1923 የቱርክ ሪፐብሊክን መስርቶ  የመጀመሪያው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነ።

ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ንጉሣዊውን ሥርዓት በማስወገድ  የስልጣን መንበሩን  ካፀኑ በኋላ  ሀገሪቱን ለዘመናት ወደኋላ ሲጎትታት  የነበረውን  የኦቶማን ሥርዓት በማላቀቅ  በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድትከበርና እንድትጠነክር የሚያስችላትን  ሥር-ነቀል ለውጦችን ተግባራዊ አደረገ።

በምርጫ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ እንዲሰፍን ማድረግ፣ ሃይማኖትንና የፖለቲካን ሥርዓትን መለየት፣ የተርክዬን ብሔራዊ ማንነትና ወሰን በማጠናከር በዘር ከተከፋፈለች ቱርክ ይልቅ በብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተች ጠንካራ ሀገር  መፍጠር ዓላማው አደረገ።

ሀገሪቱ በኢንዱስትሪና በኢኮኖሚ እንድትጠነክር በማሰብ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት መንግሥት በዋና ዋናዎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ ከፍተኛ ሚና አንዲጫወት የሚያደርግ ዋና ዋና ለውጦችን እንዲተገበሩ አድርጓል።

በዚህ መልኩ ቱርክን ለመቶ ዓመታት ወደኋላ ሲጎትታት ከኖረው የኦቶማን  አገዛዝ በማላቀቅ  በጠንካራ መሰረት የቆመችውን ዘመናዊ ሀገር የፈጠረውና  ለአሁኗ ተርኪዬ መመስረት ታላቅ አስተዋፅኦ ያበርከተው መሪ ዘላለም ሲታወስ በቱርካውያንም ዘንድ የዘመናዊቷ ተርኪዬ መስራች ሆኖ ይታወሳል።

በየዓመቱም ህዳር 1 (November 10, 1938) ከዚህ ዓለም በሞት የተለየበትን ቀን በመላው ተርኪዬ የመታሰቢያ በዓል ሆኖ ይከበራል።

በዚህ እለት በተርኪዬ ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ያሉ ዜጎች በትምህርት ቤቶች  በመንግሥትና በግል ተቋማት ሥራና ትምህርታቸውን በማቆም ለሁለት ደቂቃ ያህል የህሊና ፀሎት በማድረግ የተርኪዬን ባለውለታ እና መሰረት ጣይ መሪ ያስባሉ።

ቱርካውያን ችግሮች ቢያጋጥሟቸው እንኳ የሚሰባሰቡበት የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም የሚመዝኑበት የታሪክም የፖለቲካም መለኪያቸው መሰረቱ የዛሬዋ ቱርክ መስራች እነሱ አባታችን የሚሉት ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ነው።

የብዙ ሺህ ዘመናት ገናና ስላጣኔ ባለቤት ቢሆኑም፣ የዛሬዋን ገናና ቱርክ የሰጣቸው መሪያቸው ከቁልቁለት እና ከመጥፋት ያወጣቸው ነውና የቱርካውያን ሁሉ ልኬታቸው አድርገውታል።

የኋላ ታሪካቸው እጅግ ብዙ ነው። ግን ያን የሚያክል ግዙፍ ሀገር እና ኢምፓየር ለማጣት እኔ ቱርካዊ ነበርኩ ማለት ብርቅ ሊሆን ጫፍ ሲደርስ እንደብርሃን በቅጽበት ሀገር ሰርቶ የትብብር እና የአንድነት መንገዱን አሳይቶ ዛሬ ቱርካውያን የስልጣኔ ጎዳናቸውን ተያይዘውታል።

በዋሲሁን ተስፋዬ