Search

የትውልድ ቅብብሎሽ ተምሳሌት የሆነው ‘ሳግራዳ ፋሚሊያ’

ሓሙስ ኅዳር 04, 2018 780

ስፔናውያንሳግራዳ ፋሚሊያ’ ወይም "የቅዱስ ቤተሰብ ቤተመቅደስ" ይሉታል። በባርሴሎና ውስጥ የሚገኝ የዓለማችን አስደናቂ የሮማ ካቶሊክ ባሲሊካ ነው።

ይህ የባለ ራዕዩ አርክቴክት አንቶኒ ጋውዲ ድንቅ የንድፍ ሥራ ውጤት የሆነው ቤተክርስቲያን የተጀመረው የዛሬ 143 ዓመት ሲሆን፣ ዛሬም በቅብብሎሽ እየተሠራ ይገኛል። ጋውዲ የመጨረሻዎቹን 40 ዓመታት ዕድሜውን ለባሲሊካው ሥራ ብቻ ሰጥቶ ኖሯል።

በታሪክ ውስጥ በጣም ዝነኛ እና ውስብስብ ከሆኑት የሥነ-ሕንፃ ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን፣ ተፈጥሮን ማዕከል አድርጎ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የንድፍ ሳይንስ በሆኑት ጎቲክ እና አርት ኑቮ የንድፍ ዓይነቶች ቅይጥ የተሠራ ሕንፃ ነው።

ባርሴሎናዎች ከኃያሉ ክለባቸው ቀጥሎ የሚኮሩበት ውበታቸው ነው -ሳግራዳ ፋሚሊያ’። በርካት ቱሪስቶችን በመሳብ ቀዳሚ ከሆኑት ቦታዎች አንዱ ነው።

ማንም ሰው ወደ ሕንፃው ውስጥ ሲገባ ግዙፍ ዛፎች በሚመስሉ አምዶቹ እና ሥልታዊ በሆነ መንገድ በተሠሩ ባለቀለም የመስታወት መስኮቶች በሚፈጠረው ብርሃን ተደንቆ አያባራም። የንድፍ ሳይንስን ከተፈጥሮ ጋር አጣምሮ የተሠራ ያሰኘውም ይኸው አስደናቂ ውበቱ ነው። 

ይህ የአንቶኒ ጋውዲ የሥነ-ሕንፃ ድንቅ ራዕይ ውጤት የሆነው ፕሮጀክት የትውልድ መናበብን ያስመሰከረ ፕሮጀክት ነው። የትውልድ ቅብብሎሽ ተምሳሌታዊነቱ ልዩ የሆነውሳግራዳ ፋሚሊያ’ ወጪው ሙሉ በሙሉ የተሸፈነው ከሕዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ሲሆን፣ ይህም መደጋገፍ እና የጋራ ሕልምን አመላካች ነው። 

ማንኛውም ሥራ በትውልድ ቅብብሎሽ ከተሠራ የሐሳብ ምንጭ እና የጋራ እሴት መገለጫ እንደሚሆን ይህ ፕሮጀክት ማስተማሪያ ሊሆን የሚችል ነው።

በተለይም ረጅም ጊዜ መውሰዱ ሳያሰለች ከመቀጠሉም በላይ በሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮች የተፈቱባቸው መንገዶች በመመካከር ችግሮችን እየፈቱ መሄድ እንደሚቻል የምንማርበት ሥራ ነው። እንደዚህ በመመካከር እና በመናበብ የተሠራው ሥራ ዛሬ ከስፔን አልፎ ዓለም የሚደመምበት ሆኗል። ሀገርም እንደዚህ ነው የሚገነባው።

ጋውዲን ጨምሮ ስምንት አርክቴክቶች በሥራው የተሳተፉበት ፕሮጀክቱ ባለፉት 143 ዓመታት የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ ነው እዚህ የደረሰው፡-

የመጀመሪያዎቹ ዓመታት እና የጋውዲ ራዕይ (1882–1926)

የፕሮጀክቱ ሐሳብ የመጣው "ቅዱሱ ቤተሰብ" ቤተ መቅደስ ለማሠራት በፈለጉት የመጽሐፍት ነጋዴው ጆሴፕ ማሪያ ቦካቤላ ቤተሰብ ነበር። ሐሳቡ ተቀባይነት ሲያገኝም 1882 በፍራንሲስኮ ፓውላ ዴል ቪላር አማካኝነት ሥራው የኒዮ-ጎቲክ ንድፍ (Neo-Gothic style) መሠረት በማድረግ ተጀመረ። ግንባታው ከተጀመረ ከዓመት በኋላ ሕንፃው አሁን ላለበት አስደናቂ ውበት ያበቃው አንቶኒ ጋውዲ ዋና አርክቴክት ሆኖ ሥራውን ጀመረ።

ጋውዲጎቲክ’ (Gothic) እናአርት ኑቮ’ (art nouveau) የተሰኙ የንድፍ ዓይነቶችን ከተፈጥሮ ጋር በማዋሃድ ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ የዛፍ ቅርጽ ያላቸው አምዶችን (Arboriform) እና ጠመዝማዛ ጂኦሜትሪን በመጠቀም በዓለም ላይ ልዩ የሆነውን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ።

ጋውዲ ቤተመቅደሱን የነደፈው ሦስት ሐውልቶች እና የተለያየ ከፍታ ያላቸው 18 ማማዎች እንዲኖሩት አድርጎ ሲሆን፣ 12 ሐዋርያት፣ የአራቱ ወንጌላውያን፣ የቅድስት ማርያም እና የኢየሱስ ክርስቶስ (ከሁሉም ረጅሙ) ቅርጾችን አካትቶበታል።

1914 ጀምሮ 1926 ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት ጊዜ ድረስ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለፕሮጀክቱ ብቻሰጠ ሲሆን፣ እዚያው ቅርብ ሆኖ እየተከታተለ በመጨረሻም ከሕንፃው ክፍል የክርስቶስ ልደትን የሚያሳየው ቅርጽ ብቻ ተጠናቅቆ በማየት እረፍቱ በዚያው ሆኗል።

ቀውስ እና ትንሣኤ (1926–1980ዎቹ)

የጋውዲ ሞት እና ከዚያ በኋላ በስፔን ውስጥ የተከሰተው ግጭት ለፕሮጀክቱ ቀጣይነት ትላልቅ ፈተናዎች ነበሩ። ጋውዲ 1926 ሲሞት የተጠናቀቀው የባሲሊካው 15-25 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ እሱ ሲያርፍ ደቀ መዝሙሩ ዶሚኒክ ሱግራኔስ ሥራውን ተረከበ።

1936 በሀገሪቱ በነበረው የከፋ ግጭት የካታላን አናርኪስቶች የጋውዲን የመጀመሪያ ንድፎች፣ ሥዕሎች እና የፕላስተር ሞዴሎችን አውድመውት ነበር። ይህም ለአራት አሥርተ ዓመታት የተለፋበትን ሥራ ወደኋላ በመመለሱ አርክቴክቶች የመጀመሪያውን ሐሳብ ለማግኘት ቁርጥራጮችን እና ፎቶግራፎችን በማሰባሰብ እንዲሁም በሥራው ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎችን በማነጋገር ንድፉን እንደ አዲስ እንዲጀምሩ አስገድዷቸዋል።

የእርስ በርስ ግጭቱ ሥራውን በከፍተኛ ሁኔታ ቢያጓትተውም ጆሴፕ ማሪያ ሱቢራችስ በጠንካራ እና የማዕዘን ቅርፃቅርፅ ዘይቤ የሚታወቀውን የክርስቶስ ስቃይ እና ስቅለትን የሚያሳየውን ቅርጽ 1954 ጀምሮ 1976 አጠናቀቀ። 

ዘመናዊው እና የመጨረሻ ደረጃዎች (1980ዎቹ እስከ አሁን)

20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ እና 21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች መዘመናቸው እና የገንዘብ ድጋፉም እየጨመረ መምጣቱ ግንባታው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲፋጠን አድርጎታል። 

1980ዎቹ በኮምፒዩተር የታገዘ ዲዛይን (CAD) መፈጠር አርክቴክቶች ለጋውዲ ውስብስብኦርጋኒክ ጂኦሜትሪመፍቻ እንዲያገኙ እና ወደ ሥራ እንዲመልሱት አስችሏቸዋል።

ቱሪስቶች በፕሮጀክቱ እየተሳቡ መምጣታቸው ደግሞ ለሕንፃው ግንባታ የማይቋረጥ የገንዘብ ምንጭ ሆኖታል። በውስጠኛው ክፍል ያለው ዋና መዋቅራዊ ሥራ 2010 ተጠናቀቀ ሲሆን፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16 በይፋ ለአገልግሎት ክፍት አድርገውታል።

2021 የቅድስት ማርያም ቅርጽ ተጠናቅቆ ተመርቋል። 2022 እስከ 2023 ለአራቱ ወንጌላውያን መታሰቢያ የተሠሩት አራቱ ማማዎች ተጠናቅቀዋል። በሕንፃው ማዕከላዊ ጫፍ ላይ 2025 የተጠናቀቀው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልሳግራዳ ፈሚሊያ’ን 162 ሜትር በላይ ከፍታ ያለው በዓለም የመጀመሪያው ረጅሙ ቤተ ክርስቲያን አድርጎታል።

በጉጉት የሚጠበቀው ፍፃሜው

የቤተክርስቲያኑ ዋና የመዋቅር ሥራ 144 ዓመታት በኋላ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም የግንባታው ታሪካዊ ፍፃሜ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።

የቤተክርስቲያኑን ከፍታ ወደ 172 ሜትር እንደሚያደርስ የሚታሰበው የኢየሱስ ክርስቶስ ቅርጽ የጋውዲን ዕረፍት መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ 2026 ፍፃሜውን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ዋናው መግቢያ አካባቢ ሊሠራ የታሰበው ሰማይን እና ዘላለማዊ ክብርን የሚወክለው ሥራ እና ሌሎች የመጨረሻዎቹ ቅርጻ ቅርጾች እንዲሁም በዙሪያው ያሉት ጌጣጌጦችን ጨምሮ አጠቃላይ ሥራው ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ 2034 አካባቢ ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ ተይዞለታል።

ሕንፃው ከኮሎኝ ካቴድራል (632 ዓመታት) ሚላን ካቴድራል (600 ዓመታት) እና ፕራግ ከሚገኘው ቅዱስ ቪተስ ካቴድራል (600 ዓመታት) የተጠናቀቁ ግንባታዎችን ተከትሎ በግንባታ ሂደት ላይ በመቆየት አራተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያደርገዋል።

መቶ ዓመታትን ተሻግሮ ሳይጠናቀቅ የዚህ ዘመን ትውልድ የተመለከተው ብቸኛ ሥራ ደግሞ ሳግራዳ ፋሚሊያ ይሆናል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #SagradaFamilia #Barcelona