Search

በሩሲያ ከ500 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈነዳው እሳተ ገሞራ

በሩሲያ ሩቅ ምሥራቅ በምትገኝ ደሴት ከ500 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መፈንዳቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ሳምንት ከተከሰተው ርዕደ መሬት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ተናግረዋል።
 
ባለሙያዎቹ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በሩሲያ በሬክተር ስኬል 8.8 ከተመዘገበው ርዕደ መሬት በኋላ ለበርካታ ሳምንታት ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር።
 
የሩሲያ የድንገተኛ አደጋ ሚኒስቴርም በአካባቢው በተከሰተው እሳተ ገሞራው ሳቢያ ከፍተኛ ጭስ ሲወጣ የሚታይ ቢሆንም፣ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ምንም አይነት ስጋት አለመኖሩን አስታወቃል።
 
ትላንት እሁዱ ከእሳተ ገሞራ ፍንዳታው ከሰዓታት በኋላ በሬክተር ስኬል 7.0 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ የኩሪል ደሴቶችን መምታቱንም የሩሲያ የድንገተኛ አደጋ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ የሩሲያ የዜና ወኪል አር አይ ኤ ዘግቧል።
 
ይህን ተከትሎ የተነሳው ሞገድ ዝቅተኛ ቢሆንም ማዕበል ሊያስከትል ስለሚችል በካምቻትካ ሦስት አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች አሁንም ከባሕር ዳርቻው መራቅ እንዳለባቸው ተነግሯል።
 
ሁለቱም ክስተቶች ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ስፍራ ከተከሰተው ርዕደ መሬት ጋር የተገናኙ ሊሆኑ ይችላሉ የተባለ ሲሆን፤ ይህም እስከ ፈረንሳይ ፖሊኔዥያ እና ቺሊ ድረስ የሱናሚ ማስጠንቀቂያዎችን እንዲሰጡ አድርጎ ነበር።