የሰው ልጅ ስልጣኔ እና ዕድገት ከተፈጥሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። የቀደሙት ስልጣኔዎች አንድም ከወንዞች አሊያም ከባሕር በቅርበት ላይ የመሆናቸው አንዱ ምስጢርም ይሄው ነው። የዓለማችን ታላላቅ ስልጣኔዎች የነበሩት እና አሁንም የስልጣኔ ባለቤቶች የሆኑ ሀገራት ከውሃ ጋር የተገናኙ ሆነው ነው የምናገኛቸው። ለዚህም ነው የኪነ-ጥበብ ሰዎች የወንዞቹን አስተዋጽኦ በተለያዩ መንገዶች የገለጿቸው፡፡ ወንዞቹ በኪነ-ጥበብ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት ድርሳናትም ጭምር ነው የተጠቀሱት፡፡ እስቲ የዓለም ስልጣኔ መነሻዎች እና የወንዞችን ታሪክ በጥቂቱ እንመልከት፦
1. ዓባይ
የጥንትም ሆነ ዘመናዊ ጸሐፊዎች አራት ዋና ዋና ወንዞችን "የዓለም ሥልጣኔ መነሻ" ናቸው በማለት ይጠሯቸዋል፡፡ የመጀመሪያው የእኛው ዓባይ ነው፡፡ ግሪካዊው ሄሮዶተስ ዓባይ ከደጋማው የኢትዮጵያ ምድር የሚያደርስላትን ግብፅን "የዓባይ ስጦታ" ይላታል፡፡ ለዚህም ነው ዓባይ የጥንት ግብፃውያን የሥልጣኔ ምንጭ እንደሆነ የሚነገርለት፡፡
ኢትዮጵያውያን አባቶች ዓባይን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው ‘ግዮን’ ነው ይሉታል፡፡ ገነትን ከሚያጠጡት አራቱ ወንዞች አንዱ ኢትዮጵያን የሚከብበው ስም ግዮን እንደሚባል ተጠቅሷል፡፡ ይህም በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ቁጥር 13 ላይ "የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል" በሚል ተጠቅሷል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም ነው ሰከላ በሚገኘው የዓባይ ምንጭ ላይ ቤተ መቅደስ የተሠራው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ሲመረቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ “ለዘመናት ኢትዮጵያን ቋሚ አድርገው ካቆዩ ዐምዶች መካከልም ፈለገ ግዮን የተባለው የዓባይ ወንዝ እና 'ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች' የሚለው የተስፋ ቃል እንደሆነ የታመነ ነው” ማለታቸው ለዚህ እምነት መረጋገጫ ነው።
አክለውም፣ "የኢትዮጵያ ትዕምርት ተደርጎ የሚወሰደው ፈለገ ግዮን በእኛ ዘመን ለሕዝቡ ብርሃን እያበራ አገልግሎት መስጠት የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ በማየታችን ከሁሉ አስቀድመን ለእግዚአብሔር አምላካችን ምስጋና እናቀርባለን" በማለት ዓባይ የኢትዮጵያ ተስፋ መሆኑን አረጋግጠዋል።
2. ጤግሮስ እና ኤፍራጥስ
ሲጠቀሱ የማይለያዩት ጤግሮስ እና ኤፍራጥስ የገናናው ሜሶፖቶሚያ ሥልጣኔ ምንጮች ናቸው፡፡ የእብራውያን መጽሐፍ የሆነው ቶራ ወንዞቹን ‘የኤደን ገነት የአትክልት ስፍራዎች’ ይላቸዋል፡፡ የጥንት ግሪክ ጸሐፊያንም ሜሶፖቶሚያን ‘በወንዞች መካከል የሚገኝ የምድር ገነት’ ይሉታል፡፡ የዓለማችን የመጀመሪያው ጽሑፍ (ኩኒፎርም) መገኛ እነዚህ ወንዞች ናቸው፡፡ የከተሞች፣ የሂሳብ እና የመጀመሪያዎቹ የህግ ኮዶች (የሃሙራቢ ኮድ) መፈጠሪያም እነዚሁ ወንዞች ናቸው። ወንዞቹ "ገነትን ያጠጣ ዘንድ ወንዝ ከኤደን ፈሰሰ፤ በዚያም በአራት ወንዞች ተከፈለ። የሦስተኛው ወንዝ ስም ከአሦር በስተምሥራቅ የሚፈሰው ጤግሮስ ነው። አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው" በማለት ዘፍጥረት 2፣ 10-14 ላይ የተጠቀሱት።

3. ኢንዱስ
የኢንዱስ ወንዝ ምስጢራዊ ከምትባለው እና በእስያ ውስጥ ከምትገኘው ቲቤት አምባ የሚመነጭ ነው፡፡ በሂማሊያ በኩል አድርጎ ወደ ዓረቢያን ባሕር ከመግባቱ በፊት በደቡብ ምዕራብ ፓኪስታን በኩል የሚያልፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ነው። ወንዙ ለፓኪስታን እና ለህንድ የሕይወት ምንጫቸው ነው፡፡ በ1960 በሁለቱ ሀገራት መካከል በተፈጸመ የውኃ መጋራት ስምምነት የሚተዳደር ነው። ኢንዱስ ወንዝ የኢንዱስ ሸለቆ (የሃራፓን ሥልጣኔ) ምንጭ ነው፡፡ እንደ ‘ካህኑ-ንጉሥ’ እና ‘የዳንስ ልጃገረድ’ ያሉ ታሪኮችን የያዙ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾች፣ ውስብስብ ማህተሞች፣ የሸክላ ዕቃዎች እና ጌጣጌጦች በአካባቢ መገኘታቸው ወንዙ የጥንት ሥልጣኔ መገኘ እንደነበር ምሥክሮች ናቸው። ‘ሃራፓ’ እና ‘ሞሄንጆ-ዳሮ’ የተባሉ በጣም የተራቀቁ እና ወጥ በሆነ መልኩ የታቀዱ የከተማ ማዕከላት በመዘርጋ ከሜሶፖቶሚያ ጋር ሰፊ የንግድ ልውውጥን ሲደረግበት የነበረ መስመር እንደሆነም ተመራማሪዎች የደረሱበት ነው።
4. ቢጫ ወንዝ
ቢጫ ወንዝ (Yellow River) የጥንታዊቷ ቻይና የሥልጣኔ ምንጭ ነው፡፡ ሲማ ኪያን የተባለው ታላቅ የቻይና ታሪክ ምሁር ስለ ወንዙ በስፋት የጻፈ ሰው ነው፡፡ ቢጫ ወንዝ (Huang He) "የቻይና ሥልጣኔ መገኛ" በመባል ይታወቃል፡፡ ወንዙ በተደጋጋሚ የሚፈጥረውን ጎርፍ ለመቋቋም የተሠሩ ሥራዎች የሰው ልጆችን ብቃት ያሳዩም ነበሩ፡፡ ይህም በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ግዙፍ ሕዝባዊ እቅስቃሴ እና የተማከለ የቁጥጥር ሥርዓትን መፍጠር እንዲቻል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የቻይና ቀደምት ሥርዎ መንግሥታት መነሻም በዚሁ ወንዝ አካባቢ የተፈጠሩ ሥልጣኔዎች እንደነበሩ በታሪክ ሰፍሯል።

ኢትዮጵያ እና ወንዞቿ
ኢትዮጵያውያን ታሪክ ጸሐፊዎች እና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ለኢትዮጵያን ወንዞች ተቀኝተዋል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን አዋሽን፣ ጸሐፌ ተውኔት ጌትነት እንየው ዓባይን አስመልክተው የሠሯቸው ሥራዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በሥነ-ቃሉ ቁጭቱን፣ ተስፋውን እና ፍቅሩን መግለጽ ልማዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለወንዞቹ ተቀኝቷል፡፡ አብዛኛው ሥነ-ቃሎች እና ቅኔዎች ግን የቁጭት ነበሩ፡፡ በተለይም በዓባይ ላይ ለዘመናት ሲነገሩ እና ሲጻፉ የነበሩት ቁጭቶች ኢትዮጵያ በወንዞቿ መጠቀም አለመቻሏን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ዓባይ ያሉ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት የሚያጠጡ በርካታ ታላላቅ ወንዞች ምንጭ በመሆኗ ኢትዮጵያ ራሷን ባትጠራም ሌሎች ግን "የአፍሪካ የውኃ ማማ" ነች እያሉ ይጠሯታል። 12 የሚሆኑ ታላላቅ ወንዞች ያሏት ኢትዮጵያ፣ ከአዋሽ በስተቀር ሁሉም ወንዞች ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚፈስሱ ናቸው።
እነዚህ ወንዞች ግን የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጭ ከመሆን ይልቅ ችላ በመባላቸው ያኮረፉ ይመስል አፈሯን ለሌላ ይዘው ሲጓዙ ኖረዋል፡፡ ለም አፈሯን የለመዱትም ኢትዮጵያ ነቅታ ከወንዞቿ ጋር አንዳትታረቅ ሴራ ሲጎኖጉኑ ኖረዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ከወንዞቿ ጋር እየታረቀች ነው፡፡ ጊቤ ብርሃን እየሰጠ ነው፤ ዓባይ የብርሃን ዘመንን ሊያፈካ ሥራ ጀምሯል፤ አዋሽ የአፋርን ምድር እያለመለመ ነው፤ ዋቢ ሸበሌ ‘እኔ እያለሁ አንዴት ኢትዮጵያ ትራብ!’ በሚል ቁጭት ኢትዮጵያን ሊመግብ የተነሳ መስሏል፡፡ የዓባይ ልጆች ታሪክን በመቀየራቸውም የቁጭት እንጉርጉሮ እና ቅኔውም ወደ ተስፋ ተቀይሯል።
አሁን ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ ነኝ ብላ ራሷን ለመጥራት የማሰቢያው ጊዜም እየመጣ ይመስላል። ምክንያቱም ሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያ ውሃ መቼ ቸግሯት እንደልቧ ከሰማይም ከመሬት ስርም የሚፈልቅላት ናት የሚለው ስም በአንዱም ወንዞቿ የመጠቀም ፍላጎቷን በዓለም እየገደበ የመጣ ትርክት ሆኖ ቆይቷል። ዛሬ ላይ ግን ይህ ትርክት ተቀይሮ ኢትዮጵያ የራሷን ወንዞች የመጠቀም ፍላጎቷ በተግባር እየተገለጠ የሚሄድበት ዘመን ጀምሯል።
በለሚ ታደሰ