ደቡብ ኮሪያ በሰሜን ኮሪያ ድንበር ላይ ለ62 ዓመታት የነበሩትን የድምጽ ማጉያዎች ማንሳት ጀምራለች፡፡
ድምጽ ማጉያዎቹ ለነዚህ ሁሉ ዓመታት ፀረ-ሰሜን ኮሪያ ፕሮፖጋንዳ ሲያስተላልፉ የነበሩ ናቸው።
ከ1963 ጀምሮ ፊታቸውን ወደ ሰሜን ኮሪያ አዙረው ድንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩት እነዚህ ድምጽ ማጉያዎች፣ ፀረ-ሰሜን ኮሪያ የሆኑ መልዕክቶችን የያዙ የተለያዩ ፕሮፖጋንዳዎችን ፣ሙዚቃዎችን እና ዜናዎችን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
ሁለቱ ሀገራት ከ1950ዎቹ ጀምሮ ውጥረት ውስጥ የቆዩ ሲሆን፣ አዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚደንት ጃይኢ ምየንግ በሀገራቸውና በሰሜን ኮሪያ መካከል ያለውን የጠላትነት ስሜት ለመቀነስና በሂደትም ለመወያየት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ እነዚህ ድምጽ ማጉያዎች ስርጭታቸውን አቋርጠው የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ተተክለው ከቆዩበት ቦታ መነሳት መጀመራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ በተመሳሳይ እንደነዚህ አይነት ድምጽ ማጉያዎች ያሏት ሲሆን የደቡብ ኮሪያን ስርጭት ማቆም ተከትሎ በተመሳሳይ የፀረ-ደቡብ ኮሪያ ፕሮፖጋንዳ ማሰራጨቷን አቁማለች።