Search

የሃይማኖት ተቋማት ግጭቶችን የመፍታት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው - የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ

4ኛው አገር አቀፍ የሰላም ጉባዔ በሐረር መካሄድ ጀምሯል።

ጉባዔው "ሃይማኖት ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ ነው መካሄድ የጀመረው።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፥ የእርስ በእርስ ግጭቶችን ለማከም የሃይማኖት መሪዎችና የእምነት ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የሰላም ኮንፍረንሱ ሃይማኖቶች ለጋራ አላማ እንዲቆሙ እና የአባቶችን የመከባበር እና የአብሮነት የታሪክ አሻራ ሳይሸራረፍ ለማስቀጠል የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ዑመር በበኩላቸው፤ ሃይማኖት የሰላም የአንድነትና የአብሮነት መሰረት ናቸው ብለዋል።

የሐረሪ ክልል ይህንን የአብሮነት እሴት ከትውልድ ትውልድ በማሸጋገር ግንባር ቀደም መሆኗን አንስተው፤ ይህንን የዳበረ እሴት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል አጠናክሮ ማስቀጠል ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ እና በሐረሪ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በጋራ የተዘጋጀው የሰላም ኮንፍረንሱ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ የተለያዩ ጽሑፎች ላይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

በቴዎድሮስ ታደሰ