የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በተከበረባቸው ከተሞች ሁለንተናዊ ለውጥ እየተመዘገበ ነው ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ከክልሎች ጋር በመተባበር የሚዘጋጀው የብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን በዓል በተለይ ከለውጡ ወዲህ ዓላማውን ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

የብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲቀራረቡ እና ያላቸውን እምቅ ሀብት እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ፤ በአሁኑ ወቅት ክልሎች ያለምንም ጣልቃገብነት ራሳቸውን እና ሀብታቸውን የሚያስተዳድሩበት ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
ዘንድሮ በሚከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን፣ ዜጎች የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን እንዲያውቁት ይደረጋልም ነው ያሉት።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተደድር እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያን ከፍ አርጎ ማሳያት በሚያስችል መልኩ በዓሉን ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ከፊሉ በተጠናቀቁበት እና ከፊሉ በተጀመሩበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ትርጉም አለውም ብለዋል።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ ዓምና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ አርባምንጭ ከተማ በድምቀት መከበሩ የሚታወስ ነው።
በሜሮን ንብረት
#ebcdotstream #ethiopia #nations #nationalities #peoples