የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ዘላቂ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የባህር መዳረሻ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልጋት ገለጹ።
ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና Horn Review በጋራ ባዘጋጁት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በወቅታዊ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች እና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መድረኩ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቦች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን እና የብዙኃን መገናኛ አባላትን በአንድ ላይ ያሰባሰበ እና የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የአፍሪካ ቀንድ ዕይታዎች ላይ እና በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በማተኮር ጥልቅ ውይይት ለማድረግ ያለመ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ መድረክ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገትን እና ልማትን ለማስቀጠል አስተማማኝ የባህር መዳረሻ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የባህር በር ተደራሽነት ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከኤርትራ ጋር ስላለው ግንኙነት ሲገልጹም፣ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የጠብአጫሪነት ድርጊት ቢፈፀምባትም ከፍተኛ ትዕግሥት እንዳሳየች ጠቁመው፣ "እንዲህ ዓይነቱ ያልተገደበ ትዕግሥት ግን በዘላቂነት ይኖራል ማለት አይደለም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኤርትራ ቀጣናዊ ሰላም እና ውህደት ጋር የሚስማማ ገንቢ አካሄድ እንድትከተል እንዲያበረታታም አሳስበዋል።