Search

ሾፌር አልባ የታክሲ አገልግሎት በሳዑዲ ሊጀመር ነው

ሾፌር አልባ የታክሲ አገልግሎት 'ዊ ራይድ' በሳውዲ ዓረቢያ አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ ማግኘቱ ተነግሯል።
 
የቻይናው ሾፌር አልባ ተሽከርካሪ አምራቹ 'ዊ ራይድ' በሳውዲ ያገኘውን ፈቃድ ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ6 ሀገራት ፍቃድ የተሰጠው ብቸኛ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መሆን ችሏል።
 
የተቀሩት ፍቃድ ያገኘባቸው ሀገራት ቻይና፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ፣ ሲንጋፖር፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካ ናቸው።
 
ኩባንያው የማሽከርከር ፍቃዱን ከማግኘቱ በፊት የተለያዩ የቴክኖሎጂ ማረጋገጫዎችን ማግኘቱ እንዲሁም የደህንነት ፍተሻ ደረጃዎችን ማለፉ ተገልጿል።
 
የ'ዊ ራይድ' ሾፌር አልባ ታክሲ በሳዑዲ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ላይ በቅርቡ አገልገሎቱን መስጠት የሚጀምር ሲሆን፣ ለአካባቢው ሞቃታማ የአየር ፀባይ ተስማሚ ተደርጎ የተሰራ መሆኑን የቻይና ዴይሊ መረጃ ያመላክታል።
 
ሾፌር አልባ ታክሲው በተለያዩ ፓርኮች፣ የቱሪስት መስህብ በሆኑ ስፍራዎች እንዲሁም ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎች አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
 
በንፍታሌም እንግዳወርቅ