Search

ቱርኪዬ እና አውስትራሊያ የተፋጠጡበት የ31ኛው የአየር ንብረት ጉባዔ አስተናጋጅነት ፉክክር

እሑድ ኅዳር 07, 2018 182

የ2026 የዓለም አየር ንብረት ጉባዔን (Cop31) ለማስተናገድ እየተደረገ ያለው የሦስቱ ሀገራት ፉክክር የ30ኛውን ጉባዔ አዘጋጅ ብራዚልን ጨምሮ በርካቶችን ያስገረመ ጉዳይ ሆኗል።
ጉባዔውን ለማስተናገድ ላለፉት ዓመታት ሲፎካከሩ የነበሩት ሀገራቱ በ30ኛው ጉባዔ ላይ የሚሳተፉባቸው ድንኳኖች ጎን ለጎን ተደርገውላቸዋል።
አስተናጋጇ ብራዚል ድንኳኖቻቸውን ጎን ለጎን ያደረገችላቸው ሀገራቱ በመወያየት በፍጥነት ወደ መግባባት እንዲደርሱ በማሰብ እንደሆነ ነው ዘ ጋርዲያን ላይ ጉዳዩን አስመልክቶ የጻፈው አዳም ሞርተን የጠቆመው።
የአየር ንብረት ጉባዔ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉበት ሁነት እንደሆነ የጠቀሰው ጸሐፊው፤ ጉባዔውን የምታስተናግደው ሀገር ከተሳታፊዎች ጋር ያላትን ግንኙነት ቀላል ለማድረግ እና ከተመድ የአየር ንብረት ቢሮ ጋርም በቅርበት ለመሥራት ዕድል ታገኛለች ይላል።
Cop31ን በማስተናገድ ይህን ዕድል ለመጠቀም የሚፈልጉት እነዚህ ሀገራት እስከ አሁን መግባባት ላይ እንዳልደረሱ እና ይህ ደግሞ ለጉባዔው ተሳታፊዎች እንቆቅልሽ ሆኖ መቀጠሉ ተጠቅሷል።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ በሲድኒ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፥ የቱርክ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጣይብ ኤርዶጋን ዝግጅቱን በሜዲትራኒያን ሪዞርት ከተማ አናታሊያ ለማካሄድ ከአውስትራሊያ ይሁንታ ለማግኘት እንደጠየቋቸው ተናግረዋል።
ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ እየሆነች ያለችው ሀገራቸው ጉባዔውን ለማስተናገድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ለፕሬዚዳን ኤርዶጋን መግለጻቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኔዝ ለጋዜጠኞቹ ገልጸዋል።
በፓሲፊክ ውቅያኖስ ቀጣና ያሉ ሀገራት የአየር ንብረት ጉባዔን አስተናግደው እንደማያወቁ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ጊዜው እነዚህ ሀገራት በትብብር ጉባዔውን የሚያዘጋጁበት ስለመሆኑ ከፓላው ፕሬዚዳንት እና ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር መስማማታቸውን ተናግረዋል።
የቱርኪዬ ቡድን በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ድምጹን ከፍ አድርጎ እያሰማ ይገኛል። በCop30 እየተሳተፉ ያሉት የቱርኪዬ ምክትል ፕሬዚዳንት ሴቭዴት ይልማዝ ሀገራቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት በሰሜን እና በደቡብ መካከል የድልድይነት ሚና ለመጫወት ዝግጁ እንደሆነች ገልጸዋል።
ጉባዔውን ማስተናገድ ከባድ የሎጂስቲክስ እና የፖለቲካ ዝግጅት እንደሚጠይቅ የሚጠቅሰው የዜናው ዘጋቢ አዳም ሞርተን፤ የጂኦፖለቲካዊ ፍጥጫ ባየለበት በአሁኑ ወቅት ወደ 200 የሚጠጉ ሀገራትን በማስተባበር የአየር ንብረት ቀውሱን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል የማመላከት አቅምን እንደሚጠይቅ ጠቁሟል።
የምዕራብ አውሮፓ እና ሌሎች ቡድን (WEOG) አባላት ጉባዔውን አውስትራሊያ እና የፓሲፊክ አካባቢ ሀገራት በጋራ እንዲያዘጋጁ ድጋፋቸውን ሲሰጡ እንደቆዩ የጠቆመው ሞርተን፣ ተመድ ግን ጉዳዩ በስምምነት እንዲቋጭ ሀሳብ ማቅረቡን ገልጿል።
ሀገራቱ እስከሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አማራጭ ሊወሰድ እንደሚችልም ነው የተጠቆመው።
ሁለቱ ሀገራት ካልተስማሙ የተመድ የአየር ንብረት ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ የሆነችው ጀርመን ጣልቃ እንድትገባ እየተጠየቀ ሲሆን፣ የጀርመን መንግሥት ግን የተሻለው አማራጭ ሀገራቱ ከስምምነት እንዲደርሱ ማበረታታት እንደሆነ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ 32ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (COP32) ለማዘጋጀት የተመረጠች ሲሆን፤ 31ኛውን ጉባዔ ለማዘጋጀት እየተፎካከሩ ያሉት ቱርኪዬ እና አውስትራሊያም በኢትዮጵያ መመረጥ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ