የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰኔ 2016 እስከ ሰኔ 2017 ዓ/ም ያለውን ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ መሻሻል ማሳየቱን የገለጸ ሲሆን፤ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ መሆኑንም ጠቁሟል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በሰጡት መግለጫ፥ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ መሻሻል መኖሩን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሳይቀሩ እውቅና የሰጡት ነው ያሉ ሲሆን፤ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለመኖራቸው አንስተዋል።
በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ አዎንታዊ እንድምታ ያላቸው ቁልፍ ተግባራት መከናወናቸውንም ነው የጠቆሙት።
ከነዚህም መካከል በሽግግር ፍትህ ፖሊሲው የተመላከቱት ዋና ዋና ተቋማት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ መፅደቅ፤ የዓለም አቀፍ ወንጀሎች ረቂቅ አዋጅ መፅደቅ እንዲሁም የሀገራዊ ምክክር ሂደት እና አጀንዳ ማሰባሰብ ተጠናክሮ መቀጠል በአዎንታዊ የተነሱ ናቸው።
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ መሆኑን የገለፁት ዋና ኮሚሽነሩ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ንፁሀን ቆስለዋል፣ተፈናቅለዋል እንዲሁም ሞተዋል ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና ጃል ሰኚ ነጋሳ በተባለው ግለሰብ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ወይም ኦነግ ሸኔ አባላት ጋር የሰላም ስምምነት መደረጉ በክልሉ የተወሰኑ ዞኖች ላይ የፀጥታ መሻሻል እንዳመጣ ተመላክቷልም ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ።
ሙሉ በሙሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከላከል የሚቻለው ለጥሰቱ አጋላጭ ሁኔታዎችን በመቀነስ ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ የታጠቁ ኃይሎች ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል።
በመስከረም ቸርነት