Search

በዶናልድ ትራምፕ የቀረበው የጋዛው የሰላም ስምምነት በጸጥታው ምክርቤት ድጋፍ አገኘ

ማክሰኞ ኅዳር 09, 2018 148

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት፣ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን ባለ 20 ነጥብ የጋዛው የሰላም ስምምነት ላይ ድምጽ በመስጠት በአብላጫ ድምጽ ውሳኔውን አጽድቋል።
በስምምነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ የተካተቱት አፋጣኝ ተኩስ አቁም፣ ሀማስ የያዛቸውን ታጋቾች መለቀቅ፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሰርጥ መውጣት እና ፍልስጤማውያን እስረኞችን መለቀቅ ከሞላ ጎደል ተተግብረዋል።
ጋዛን መልሶ መገንባት፣ በትራምፕ የሚመራ ከፖለቲካ ነጻ የሆነ የፍልስጤም ኮሚቴ ጋዛን ማስተዳደር እንዲሁም የሰላም ስምምነቱን የሚቆጣጠር ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ በጋዛ ማሰማራት የሚሉት በትራምፕ የቀረቡ ዋና ዋና ነጥቦች ናቸው።
በዶናልድ ትራምፕ የሰላም ስምምነት መርሆች ላይ የጸጥታው ምክርቤት ይስማማ እንጂ በጋዛ ሰርጥ የሚገኘው ሀማስ ሙሉ በሙሉ በሀሳቡ አልተስማማም፤ ሀማስ በጋዛ ስለሚኖረው ቆይታ ማረጋገጫ ይፈልጋል ተብሏል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታሪክ ውስጥ ከታዩ ታላላቅ ስብሰባዎች እና ውሳኔዎች አንዱ ነው ሲሉ ስብሰባውን ገልጸውታል።
በተጨማሪም ወሳኔው እንዲጸድቅ ድምጻቸውን ለሰጡ ሀገራት እና ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክርቤት ዶናልድ ትራምፕ ምስጋና ማቅረባቸውን አናዶሉ ዘግቧል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ