Search

“ከኢትዮጵያውያን የተማርኩት ትልቁ ነገር በራስ መተማመንን እና መቻልን ነው”፦ የቀድሞዋ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር

ማክሰኞ ኅዳር 09, 2018 171

የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ (ዶ/ር)፣ ስለኢትዮጵያውያን በራስ የመቆም እና የመቻል ተምሳሌትነት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምስክር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“ከኢትዮጵያውያን የተማርኩት ትልቁ ነገር በራሳቸው ማድረግ እንደሚችሉ ማመናቸውን ነው፤ ለዚህ ትልቁ ምክንያት ደግሞ አዕምሯቸውን ከቅኝ ግዛት እሳቤ ነፃ ማድረጋቸው ነው” ብለዋል።
ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ (ዶ/ር) በቅርቡ “አፍሪካውያን አዕምሯቸውን ከቅኝ ግዛት እሳቤ ማላቀቅ አለባቸው” በሚል መነሻ ሐሳብ በሰጡት አስተያየት፣ ኢትዮጵያውያን የሕዳሴ ግድብን ለመገንባት የውጭ እጅን አልተመለከቱም፤ ከዚህ ብዙ ልንማር ይገባልም ሲሉ ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ ዜጎች ያላቸውን በማዋጣት ያለ የትኛውም የውጭ አካል ተሳትፎ በራስ አቅም ይህን ትልቅ ፕሮጀክት እውን አድርገውታል፤ ተጠቃሚም መሆን ጀምረዋል ብለዋል።
"አብዛኞቻችን አሁንም የውጭ እጅ እየጠበቅን ነው፤ የውጭ እጅ ባንጠብቅ እና እንደ ኢትዮጵያውያን አዕምሯችንን ነፃ ብናደርግ የልፋታችንን ውጤት እናገኝ ነበር" ሲሉም ቁጭታቸውን ገልጸዋል።
ስለዚህ አሁንም ቢሆን የውጭ እጅ መጠበቁ ይብቃን፣ በምንችለው አቅም ልክ ለራሳችን ዕድገት ልንተጋ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሰለሞን ከበደ