Search

የፀና ሰላም እና የቀና ሥርዓት - የኢትዮጵያ የስምንት ዓመታት ያልተቋረጠ ጥረት

ረቡዕ ሚያዝያ 21, 2018 81

ኢትዮጵያ ካለችበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና ውስብስብ የታሪክ ሂደት አኳያ፣ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የሕልውናዋ መሠረት ሆኖ ይገኛል።

ሀገራችን ለዘመናት ከከፋፋይ ትርክቶች፣ ከውስጥ ፖለቲካዊ መዋቅር ድክመቶች እና ከጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻዎች የሚመነጩ የሰላም ፈተናዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች።

በተለይም የታሪክ ትርክቶች ወጥ የሆነ ሀገራዊ መግባባት ከመፍጠር ይልቅ፣ አንዱን ወገን ባለቤት ሌላውን ደግሞ ባዕድ የሚያደርጉ ጽንፈኛ አመለካከቶች እንዲነግሡ በማድረጋቸው፣ ለውስጣዊ ግጭቶች መባባስ እንደ ማገዶ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱ ይታወቃል።

የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ከመፈታት ይልቅ ወደ ኃይል አማራጭ እንዲያመሩ ያደረገው ደግሞ ጠንካራ እና ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት አለመኖራቸው ሲሆን ይህም የሰላም እጦቱን ሥር የሰደደ ችግር አድርጎታል።

ከዚህ በተጨማሪ የቀይ ባሕር አቅራቢያ መሆኗ እና የዓባይ ወንዝ ምንጭነቷ፣ ታሪካዊ ጠላቶች በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ እና በሀገር ውስጥ ባሉ "ባንዳዎች" አማካኝነት የጥፋት አጀንዳቸውን እንዲያስፈጽሙ በር ከፍቷል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የለውጡ መንግሥት ይህንን የታሪክ አዙሪት ለመስበር እና በሰላማዊ መንገድ የሚደረግ የፖለቲካ ውድድርን ለማስፈን በሆደ ሰፊነት ረጅም ርቀት ተጉዟል።

ሰላም ማለት የጥይት ድምፅ አለመስማት ብቻ ሳይሆን ዜጎች ያለስጋት የሚኖሩበት፣ ልማት የሚፋጠንበት እና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት የሚገነባበት መሆኑን በመገንዘብ፣ የመደመር መንግሥት የጸና ሰላምን እና የቀና ሥርዓትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።

የመንግሥት የሰላም እሳቤ አዎንታዊ ሰላምን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ሲሆን ይህም ግጭት የሌለበትን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ለግጭት መንሥኤ የሆኑ መዋቅራዊ ችግሮች እንደ ድህነት፣ -ፍትሐዊነት እና መገለል የተቀረፉበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። ይህ ጥረትም ከቀጠናዊ ሰላም ትሥሥር እና "የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ" ከሚለው መርሕ ጋር ተሣሥሮ እየተከናወነ ይገኛል።

የለውጡ መንግሥት ገና ወደ ሥልጣን እንደመጣ በሐሳብ ልዩነት ተሰድደው የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጥሪ በማቅረብ ደማቅ አቀባበል አድርጓል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው ይህ የሰላም ጉዞ፣ ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት በላይ የዘለቀውን የኢትዮ-ኤርትራ የጠላትነት ግንኙነት ወደ ወዳጅነት የቀየረ እና በጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳንም የሰላም ጥረት እንዲሳካ ያደረገ በመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት እንዲሸለሙ አስችሏል።

ሰላም ተኮር ሥራዎችን ተቋማዊ ለማድረግም የሰላም ሚኒስቴር ተቋቁሞ ችግሮችን በንግግር የመፍታት ባህል እንዲዳብር እየተሠራ ሲሆን የፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማትም ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ እንዲሆኑ ሪፎርም ተደርገዋል።

በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን የሰሜኑን ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በሰላማዊ መንገድ መቋጨት መቻሉ፣ የጦር ሜዳ ድልን ወደ ዘላቂ ሰላም የመለሰ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች የነበረው ጦርነት ቆሞ ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እና ልማታቸው እንዲመለሱ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ የዘመናት ቅራኔዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስም የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንም እየሠራ ይገኛል።

እነዚህ ሁሉ ሥራዎች የኢኮኖሚ መረጋጋትን ከመፍጠር ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምን የምታስከብር እና ተሰሚነት ያላት ሀገር ሆና እንድትቀጥል አድርገዋል።

የግጭት አዙሪቱን ሰብሮ ወደ ብልጽግና ለመሻገር የዕርቅ እና የሰላም መንገድ ምትክ የሌለው መሆኑን በማመን መንግሥት እየሠራ ሲሆን በቀጣይም ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላትን በሕግ ከመግታት ባለፈ፣ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት እና የሚያሻግር ገዢ ትርክት የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በመሆኑም ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሐሳብ የበላይነት መሆኑን በመገንዘብ፣ ልዩነቶችን ወደ ጸጋ በመለወጥ እና የጋራ ማንነትን በማጠናከር ለትውልድ የምትበቃ የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባቱ ሂደት የማይቀለበስ ታሪካዊ ግዴታ ይሆናል።

በበረከት ሽመልስ