የኢትዮጵያ የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ አፈጻጸም በበርካታ ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው የ2018 ዓ.ም (የ2025/26) የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ሪፖርት አመላከተ።
ሪፖርቱ መንግሥት ተግባራዊ ያደረጋቸው የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በገቢ አሰባሰብ፣ በዋጋ መረጋጋት እና በውጭ ንግድ ላይ ያመጧቸውን ለውጦች በዝርዝር አመልክቷል።
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ10.2 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ፈጣን ዕድገት ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትመደብ አድርጓታል።
ከዚህ ጎን ለጎን፣ ላለፉት ዓመታት የኢኮኖሚው ፈተና የነበረው የዋጋ ግሽበት ወደ 9.7 በመቶ ዝቅ በማለት ወደ ባለነጠላ አኃዝ ወርዷል።
የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያውን ተከትሎ፣ በሕጋዊ እና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው ልዩነት ወደ 12 በመቶ መጥበቡ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ይህም የወጪ ንግድን በማነቃቃት በስድስት ወራት ውስጥ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አስችሏል።
በተለይም የወርቅ ምርት 1.9 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ለውጤቱ መገኘት የላቀ ሚና ተጫውቷል። በሀገር ውስጥ ገቢ በኩልም መንግሥት 704.7 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ55.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ከድርጅቶች የገቢ ግብር የተገኘው የ92.2 በመቶ ዕድገት ለሀገራችን ካዝና መጠናከር ዋነኛው ምክንያት ሆኗል። መንግሥት በስድስት ወራት ውስጥ ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች 798.2 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ለልማት ሥራዎች ከተመደበው የካፒታል በጀት ውስጥ ከፍተኛው ድርሻ ለመንገድ ግንባታ (76.3 ቢሊዮን ብር) እና ለትምህርት ዘርፍ (42.8 ቢሊዮን ብር) ውሏል።
በተጨማሪም ለክልሎች የሚሰጠው የድጋፍ በጀት በወቅቱ መለቀቁ እና ለዕዳ ክፍያ 54.5 ቢሊዮን ብር መከፈሉ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
በሌላ በኩል በገቢ እና ወጪ መካከል የ93.5 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት መኖሩ ተገልጿል፤ ቢሆንም አጠቃላይ የሪፖርቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከመረጋጋት ባለፈ ወደ ተሻለ የማምረት እና የመላክ አቅም እየተሸጋገረ መሆኑን ነው።
መንግሥት በቀጣይ ስድስት ወራት የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱን ይበልጥ በማዘመን እና የወጪ ቅልጥፍናን በማረጋገጥ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል ማቀዱን ሪፖርቱ አመላክቷል።
በዮናስ በድሉ