ሴኔጋል አፍሪካዊ ያልሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የኤሌክትሮኒክ ቪዛ (ኢ-ቪዛ) ሥርዓት በማስተዋወቅ በኢሚግሬሽን ፖሊሲዋ ላይ ጉልህ ለውጥ ማምጣቷን አስታውቃለች።
አገልግሎቱ የሀገሪቱን የኢሚግሬሽን መሰረተ ልማት፣ አስተዳደራዊ አቅም እና በዚህ ረገድ ግልፅነት ለመፍጠር እያደረገችው ያለውን ጥረት ማሳያ መሆኑም ተጠቅሷል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዑስማኔ ሶንኮ፥ ከአፍሪካ አህጉር ውጭ ወደ ሴኔጋል የሚገቡ ጎብኚዎች የቪዛ ማመልከቻ ክፍያቸውን አስቀድመው በኢንተርኔት መክፈል እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሶንኮ ሀገሪቱ ከኢ-ቪዛ ክፍያ በግምት 60 ቢሊዮን የሴኔጋል ፍራንክ ገቢ ታገኛለች ተብሎ ይጠብቃልም ነው ያሉት።
እርምጃው የሀገሪቱን አስተዳደራዊ ደህንነት እንደሚያጠናክር፣ መጉላላት እንሚያስቀር፣ እንዲሁም ለሴኔጋል የኢሚግሬሽን አገልግሎት አሰጣጥን ቀላል እንደሚያደርገው ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ሴኔጋል ካስተዋወቀችው "ሴኔጋል በ2050" አዲሱ ብሔራዊ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ሪፎርም ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ጋር የሚናበብ እንደሆነ ተጠቅሷል።
"ሴኔጋል በ2050" ስትራቴጂ የበጀት ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ሴኔጋል በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ውስጥ ያላትን ሚና ለማጠናከር ያለመ መሆኑን የቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ መረጃ ያመላክታል።
በለሚ ታደሰ