የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመመከት የሚያስችል ጠንካራ አቅም በመፍጠር ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ባንኩ የሳይበር ደህንነት ወርን ለ2ኛ ጊዜ "ለታመነ የባንክ አገልግሎት በዜሮ ትረስት ደህንነት" በሚል መሪ ሀሳብ እያከበረ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተወካይ እና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪውቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ ከባንኩ ጠቅላላ ግብይት ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚከናወነው በዲጂታል መንገድ ነው፡፡
ባንኩ የሳይበር ደህንነት ወርን ሲያከብር ለደህንነትና ስጋት ንቁ የሆነ ባንክ በመገንባት ኤ.አይ.ን በመጠቀም አዳዲስ የሳይበር ስጋቶችን አስቀድሞ ለመለየት፣ ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ለመዘጋጀት ነው ብለዋል፡፡
የሳይበር ጥቃትና የዲጂታል ማጭበርበር ሥጋት እየጨመረ መምጣቱን በመግለጽ፣ ይህንን ለመመከት ትኩረት መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡
ዓለማችን በሳይበር ጥቃት በ2025 ዓለም ከ10 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደምታጣ የጠቀሱት አቶ ኤፍሬም ይህን ዓለም አቀፍ ችግር ለመግታት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
በብሩክታዊት አስራት