Search

የቴክኖሎጂ አብዮተኛው ኖኪያ ራሱን ያጠፋበት ቆሞቀርነት፦ ከምስረታው እስከ ገበያ መውጣት

ኖኪያ የሚባል ስም በዓለም ላይ እንዲታወቅ የሆነበት አጋጣሚ አጭር ቢሆንም ረጅም ዘመን ውስጥ የጥንካሬ እና የቴክኖሎጂ ሥም መሆኑ ግን አያጠራጥርም።

በዚሁ ልክ ደግሞ በርቶ መጥፋት፣ ነገን ሳያሳቡ ዛሬ ላይ መምከን፣ ቆሞ ቀርነት ወይም ከዘመን ጋር አለመዘመን ሲነሳ በተለይ ለቢዝነስ ሰዎች በማስተማሪያነት የሚነሳም ሥምም ነው ኖኪያ።

ከ160 ዓመታት በፊት በፊንላንድ ታምፒሪ በምትባል ከተማ ሲመሰረት ዋና መሰረቱ ወረቀት እና የወረቀት ውጤቶች ላይ በማተኮር ነበር። በእርግጥ በዚህ ወቅት ኖኪያ እጅግ ፈጣን ተቀባይነት በማግኘቱ ፊቱን ወደሌሎች ፋብሪካዎች ሲያዞር ብዙም ጊዜ አልወሰደም።

ኖኪያ የኢንደስትሪውን ዘርፍ በማስፋት አዲስ በከፈታቸው ፋብሪካዎችም የፕላስቲክ ጫማዎችንና የኤሌክትሪክ ገመዶችን (ኬብሎችን) በማምረት ቀስ በቀስ ወደኤሌክትሮኒክስ ኢንደስትሪው ዓለም  ተሸጋገረ።

በዚህም የኖኪያ ምርቶች የሆኑ የጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥኖች በፊንላንድ ገበያዎች ብቅ ብቅ ማለት ሲጀመሩ በዚህ ሁኔታ  ዓመታትን በስኬት እየተሻገረ የቀጠለው ኖኪያ በተለያዩ ምርቶቹ ድንበር ተሻጋሪ እውቅና እያገኘ ሄደ።

ጊዜው በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በእጅ የሚያዙ ስልኮች የዓለምን ህዝብ ትኩረት የሳቡበት ወቅት ነበር። እና በዚህ ወቅት ከመቶ ዓመታት በፊት ከወረቀት ተነስቶ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን በማምረት ራሱን ግዙፍ ኩባንያ ማድረግ የቻለው ኖኪያ ሞባይል ስልኮችን ወደማምረት ትልቅ ደረጃ ተሸጋገረ።

በኩባንያው የመቶ ዓመታት ታሪክ ውስጥም ከስር መሰረቱ የለወጠውና በዓለም ደረጃ ዝነኛ ያደረገው የኢንደስትሪ እመርታ ይሄው ወደ ሞባይል ስልኮች ማመረት የተሸጋገረበት ጊዜ ነው

ኖኪያ ሙሉ አቅሙንና የተመራማሪዎቹን እምቅ እውቀት ተጠቅሞ ቀላል፣ ጠንካራና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያካተቱ በወቅቱ ዓለምን ያስደንቁ የነበሩ አዳዲስ ሞዴል የሞባይል ስልኮችን ማምረት ጀመረ።

የጽሑፍ መልዕክቶችን መላክ የሚያስችሉ እንዲሁም ስኔክ የተሰኘውን በወቅቱ ተወዳጅ የነበረ የሞባይል ጌም ያካተቱ የኖኪያ ስልኮች ተቀባይነት ከሚታሰበው በላይ ሆነ።

በጥቂት ዓመታት ውስጥም የኖኪያ የእጅ ስልኮች በሚሊዮኖች እጅ የሚያዙ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ኖኪያ የምድራችን ግዙፍ፣ ታዋቂ እና ተወዳጅ ኩባንያ መሆን ቻለ።

በተለይ ኖኪያ በአውሮፓውያኑ 2003 ላይ ወደገበያ ያቀረበው 1100 ሞዴል የሞባይል ስልክ የዓለምን የሞባይል ስልክ ገበያ ተቆጣጠረው። እስከዛሬም ድረስ በምድራችን ከተሸጡ የሞባይል ስልኮች የኖኪያ 1100 ያህል ሰፊ ተቀባይነት ስልክ ያለው የለም።

እስካሁን ሪከርዱን የያዘው ይህ ስልክ 255 ሚሊዮን ሰዎች ገዝተውት ነበር። ከዚያም ከሁለት ዓመት በኋላ 2005 ሌላውን 1110 የተባለ ስልክ ለገበያ አቀረበ። ይህም አዲስ ምርት 247 ሚሊዮን ስልኮችን መሸጥ ቻለ። ይህኛውም ስልክ እስከዛሬ በብዛት መሸጥ ከቻሉ የሞባይል ስልኮች ሁለተኛ በመሆን እየመራ የሚገኝ ስልክ ነው። በዓለም ዙሪያ ኖኪያ ተወዳዳሪ የሌለው የሞባይል ስልክ አምራች መሆኑን ዳግም አስመሰከረ

ኖኪያ በዚህ በስኬት ላይ ስኬት እያስመዘገበ በሚሄድበት ወቅት ተወዳዳሪ የሆኑ የሞባይል ስልክ አምራች ኩባንያዎች የተሻለ ቴክኖሎጂ እና የአመራረት ዘዴን ይዘው በመቅረብ ኖኪያ የተቆጣጠረውን ገበያ ለመሻማት ምርምራቸውን ቀጠሉ።

በዚህ የምርምር ሥራ ውስጥ የነበረው አፕል ካምፓኒ አንደኛው ነበር።  አፕል በዚህ ለዓመታት በምስጢር ይዞ ሲያከናውን የነበረውን የሞባይል ስልኮችን ታሪክ ከስር መሰረቱ የቀየረውን ትላልቅ መስታወት (wide screen) ያላቸው ስማርት ስልኮችን ይፋ አደረገ።

እነዚህ ከኢንተርኔት ጋር መገናኘት የሚችሉ ስልኮች ወደገበያው መምጣት የሰው ፍላጎት ከኖኪያ መሰል ስልኮች ይልቅ በአዳዲሶቹ ላይ በመሆኑ ኖኪያም ገበያው መቀዛቀዝ ጀመረ።

መታት ብዙ ውስብስብ ባልሆኑ "ጠቅ ጠቅ " ስልኮች የዓለምን ገበያ ተቆጣጥሮ የነበረው ኖኪያ የቴክኖሎጂውን መዘመን ቶሎ መቀበል አልችል አለ። እዚህ ላይ በወቅቱ የነበሩ የኖኪያ አመራሮች በኖኪያ ስኬት መኩራራት እና ጊዜን በድግስ ላይ ማሳለፍ መምረጣቸው አንዱ ምክንያት ተድርጎ ይነሳል። የኖኪያ ስኬት በዓለም ላይ የናኘ ስለነበር ኖኪያን መገዳደር የሚችል ተቋም መፍጠር የሚታሰብ አይደልም ይልቁንም ትንንሽ የኖኪያ አይነት ድርጅቶች ቢመጡ እንደሁ እንጂ የሚሉ ነገን መተንበይ ያልቻሉ ሃሳቦችም ገዝፈው ኖኪያን ወረውታል። ኖኪያ የሚታደስ አለመሆኑ የገባቸው እና ቆሞ ቀርነቱን የተረዱ ተመራማሪዎች ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት ጀምረው ሌላ የነገውን ኖኪያ ለመፍጠር ሥራ ላይ ናቸው። ኖኪያም ራሱን ከዘመንና ከቴክኖሎጂ ጋር ከማዘመን ይልቅ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶባቸው በነበሩት መደበኛ ስልኮች ላይ  አተኩሮ መቆየትን መረጠ።

ኖኪያ የተለመዱትን ስልኮች እየሸጠ በነበረባቸው ዓመታት ያገኝ የነበረው ገቢ በቢሊዮን የሚቆጠር ነበር። አዳዲስ ስልኮች ይዘው ወደገበያው የመጡ ድርጅቶች ሊወዳደሩት እንደማይችሉ የተሳሳተበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ኖኪያ በገበያው ውስጥ ያለው ድርሻ ነው። የአዳዲሶቹ ስማርት ስልኮች ወደገበያ ከመጡም በኋላ ቢሆን የዓለም 50 በመቶ የሞባይል ስልኮች ገበያ በኖኪያ እጅ ስር ነበር። 2009 ኖኪያ ከተለመዱት የስልክ ምርቶቹ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት ችሎ ነበር።

ሆኖም የስማርት ስልኮች በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ኖኪያ ራሱን ከቴክኖሎጂው ጋር  ባለማዘመኑ የካምፓኒው አስደንጋጭ የቁልቁለት ጉዞ 2010 ላይ ጀመረ

በዓለም ደረጃ እጅግ ተወዳጅና ተመራጭ የነበረው ኖኪያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው ወደገበያው የተቀላቀሉትን አፕልን ሳምሰንግን መወዳደር አቃተው።

በዚህም ምክንያት በስድስት ዓመታት ውስጥ ታላቁ ኖኪያ 90 በመቶ የሚሆነው የስልክ ገበያውን በተወዳዳሪዎች ተነጠቀ።

የወረቀት ምርቶችን፣ የፕላስቲክ ምርቶችን፣ የኤሌክትሪክ ገመዶችን (ኬብሎችንና) ቴሌቪዥኖችን በማምረት ጀምሮ በሞባይል ስልኮች የዓለምን ገበያ ለዓመታት ይዞ የነበረው ኖኪያ ራሱን ማዘመን ባለመቻሉ ከሞባይል ስልክ ዓለም ራሱን ማሰናበት ግድ ሆነበት።

2014 ላይ ኖኪያ ካምፓኒ ሙሉ በሙሉ ከስሮ ለማይክሮሶፍት ኩባንያ ተሸጠ። ዛሬ ላይ የፊንላንዱ ኖኪያ ኔትወርክ ዝርጋታ ላይና 5 ቴሌኮም አገልግሎቶችን በማስፋፋት ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።

ኖኪያ በእርግጥ በድንገት ቢሆንም ታዋቂነቱን ያመጣው በሂደት ይህን ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ በዓለም ላይ ጠብቆ ለመቆየት ብዙ ሰርቷል። በሰው ልጅ የስልጣኔ ዘመን ውስጥ ስሙን በጉልህ ጽፏል። የገበያ ድርሻውም ቢሆን ቀላል ባለመሆኑ አዲስ መጥተው ሥራውን የበለጡት ድርጅቶች እንኳ ዓመታትን ፈጅቶባቸዋል።

ኖኪያ በዓመታት ውስጥ የገነባውን ዝና ለማጣት ግን ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው የፈለገው። ዛሬ ላይ ኖኪያ ከገነባው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋምነቱ ይልቅ አንድ ተቋም እንዴት በፍጥነት ካለበት ደረጃ ሊወርድ እንደሚችል ማስተማሪያነቱ ይገዝፋል። በእርግጥ ለብዙዎቹ የቴክኖሎጂ ተቋማት መፈጠር ምክንያት መሆኑ አያጠያይቅም።

እዚህ ላይ ግን አሁን ላይ ፈጣን እና ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ ራስን ከዘመኑ ጋር ማራመድ አለመቻል ራስን የማጥፋት ያህል ከባድ ውሳኔ እንደመወሰን የሚቆጠር ነው። ኖኪያም ይህን ዕጣ ፈንታ በራሱ ላይ በመወሰን በዓመታት የገነባውን ተቋም ከገበያ ውጭ ለማድረግ 6 ዓመታት ብቻ ነው ተንገዳግዶ መቆየት የቻለው።

ቆሞ ቀርነት በትክክልም የጎዳው ተቋም ቢኖር ኖኪያ ነው ለማለት ጥቂት ሰከንዶች እንኳ ማሰላሰል የሚፈልግ አይመስልም።  ዛሬ ከግለሰብ እስከ ማሕበረሰብ ከተቋም እስከ ሀገር በኖሩበት ዓለም በሚያውቁት መንገድ ብቻ መጓዝ የሚያስከፍለውን ዋጋ ከኖኪያ የሚማሩበት ታሪክ ሆኖ ተሰንዷል።