ቻይና በጤና እንክብካቤ ዘርፍ እየገጠማት ያለውን ተግዳሮት ለመፍታት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አብዮት እያካሄደች ነው።
በተለይ ከከተማ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ያለውን የጤና አገልግሎት ክፍተት ለመሙላት ያስችላሉ ተብለው እየተተገበሩ ካሉ የጤና አጠባበቅ ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎች መካከል ሰው አልባ የጤና መመርመሪያ 'ኪዮስኮች' ይገኙበታል።
እነዚህ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚታገዙ ሰው አልባ የምርመራ ኪዮስኮች ታካሚዎች ወደ ትላልቅ ከተሞች ሳይጓዙ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሲሆን ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራዎችንና የጤና ምክሮችን መስጠትም ይችላሉ።
በተለያዩ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ተቋማት ላይ እየተተከሉ ያሉት መሳሪያዎቹ ያለ ሐኪም እገዛ ካሜራዎችን እና ሴንሰሮችን በመጠቀም የሰውነት ሙቀት መጠንን፣ የደም ግፊትን፣ የኦክሲጅን መጠንን እና የልብ ምትን ጨምሮ ከ10 በላይ ወሳኝ ልኬቶችን በመውሰድ እንዲሁም ታካሚው የሚሰማውን የበሽታ ምልክቶች በመጠየቅ በአምስት ደቂቃ ውስጥ የሕክምና ውጤቱን ማሳወቅ የሚችሉ ናቸው።

በተጨማሪም በአገኙት የምርመራ ውጤት መሰረት ለቀላል ሕመሞች መድኃኒት ማዘዝና የጤና ምክሮችን መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን የቻይና መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ጠንከር ላሉ የጤና ችግሮች ሲያጋጥሙ ደግሞ ማሽኖቹ የምርመራ ውጤቱን በአቅራቢያው ለሚገኝ ሆስፒታል በመላክ ታካሚው ወደ ሆስፒታል ሄዶ ሕክምና እንዲከታተል ያደርጋሉ ተብሏል።
ቴክኖሎጂው በትላልቅ ሆስፒታሎች ያለውን ረጅም ሰልፍ እና መጨናነቅ ያቃልላል ተብሏል።
በተጨማሪ ታካሚዎች የረጅም ርቀት ጉዞ ሳያስፈልጋቸው ጥራት ያለው የጤና የምርመራ አገልግሎት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ያስችላሉ የተባሉት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ የታገዙ ሰው አልባ መመርመሪያዎች ከ95 ከመቶ በላይ ትክክለኛ ውጤት እንደሚሰጡ መረጋገጡ ተመላክቷል።
በዋሲሁን ተስፋዬ