Search

የቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተገለጠው የዲፕሎማሲ ስኬት

እሑድ ኅዳር 14, 2018 186

ኢትዮጵያ የቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔ ተጋባዥ ተሳታፊ ነች። በጉባዔው ስትገኝ ግን እንዲሁ ለተሳትፎ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን አቋም እና መልዕክት ለማንፀባረቅ ነበር። በዚሁ መሠረት በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው ታሪካዊው ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን የወል ድምጽ እና የጋራ ፍላጎት አስተጋብታለች። 

ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲፈጠር ብሎም አፍሪካ በዓለም አቀፍ ተቋማት ተገቢው ውክልና እና ድርሻ እንዲኖራት ኢትዮጵያ ጠይቃለች። ያለ ጥፋቷ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እየተፈተነች ያለችው አፍሪካ ተመጣጣኝ ካሳ እንድታገኝ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት እና በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት የአፍሪካን መፍትሔ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርባለች።

በጉባዔው ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የአፍሪካን ድምጽ ከማሰማት ባሻገር ከበርካታ የጉባዔው ተሳታፊ መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል።

የዓለማችንን ኢኮኖሚ የሚዘውሩ 20 ሀገራት በሚሳተፉበት በዚህ ትልቅ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጓቸው የጋራም ሆነ የሁለትዮሽ ውይይቶች የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማዕከል ያደረጉ ናቸው።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንኳር እሳቤ፥ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከር፣ የልማት ሀብት ማሰባሰብ፣ ኢንቨስትመንት መሳብ እናባለብዙ ወገን የዓለም ሥርዓትን ማበረታታት ነው።

ፖሊሲው የኢኮኖሚ ልማትን እና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድም ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን የሚከተል ነው። በተለይም የባሕር ተደራሽነት እና የምግብ ሉዓላዊነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ እና ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና የሚመሩ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው።

ዲፕሎማሲው የማንም ርዕዮተ ዓለም ተለጣፊ ሳይሆንባለብዙ ወገን አካሄድን ተከትሎ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማረጋገጥ የሚያስችል ነው። ከርዕዮተ ዓለም አሰላለፍ በላይ የሆነ ገቢር ነበብ (pragmatic) የውጭ ፖሊሲ አካሄድን የሚከተል ነው።

ኢትዮጵያ የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ በፖሊሲ ደረጃ ይህን አካሄድ ስትከተል የነበረ ቢሆንም፤ ተግባራዊነቱ ላይ ግን ምሉዕነት የሚጎድለው ነበር። 2010 . ወዲህ ግን የመደመር መንግሥት ገቢር ነበብ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ዲፕሎማሲው፥ የውጭ ግንኙት የሀገር ውስጥ ለውጥ እና ደኅንነት ማረጋገጫ ሆኖ ማገልገል አለበት በሚለው ፍልስፍና የሚመራ ነው።

ግቡም ሀገራዊ ልማትን ለማፋጠን ንግድ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) እና የመሠረተ ልማት ፋይናንስን ማሰባሰብ ነው።

ግቡን ለማሳካት ደግሞ ርዕዮተ ዓለሙ ምንም ይሁን ምን፣ ከምዕራብም ይሁን ከምሥራቅ፣ ከማንኛውም ሀገር ጋር መልካም ግንኙነት እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል።

ፖሊሲው፥ ባለብዙ ወገን እና አካታች ጥምረቶችን በመደገፍ በማንኛውም ሀገር ወይም ቡድን ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስም የሚሠራ ነው። ኢትዮጵያ 2024 የተቀላቀለችው ብሪክስ እና ከባሕረ ሰላጤው ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ለዚህ ማሳያ ናቸው።

ቅድሚያ ለጎረቤት የሚለውን መርሕ የሚከተለው ፖሊሲው፣ የቀጣናው እና የአፍሪካ ሰላም ለኢትዮጵያ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ ያምናል።

የኢትዮጵያ ብልጽግና ከጎረቤቶቿ መረጋጋት ጋር የተቆራኘ መሆኑን በመገንዘብ የአፍሪካ ቀንድ ከግጭት ወደ ትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነት መድረክ መሸጋገር እንዳለበት አጽንኦት ይሰጣል፤ በተግባርም ጥረትየተደረገ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራትን እና መካከለኛው ምሥራቅን እንደ አቅም እንጂ እንደ ፀጥታ ስጋት አትመለከትም፤ ነገር ግን ማንኛውም ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዲሆን ነው ሀገሪቱ የምትሻው።

ኢትዮጵያ ዓባይ እና ቀይ ባሕር የሕልውናዋ መሠረቶች እንደሆኑ ታምናለች፤ በእነዚህ ላይ ያላትን አቋም የሚጋፉ ውጫዊ ኃይሎች ሉዓላዊነቷን የሚጋፉ ስለሆኑ፣ ለእነዚህ ቀይ መስመር አላት። በመወያየት የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን ደግሞ ጎን ለጎን የምታስኬደው ጉዳይ ነው። 

በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አሁን አሁን ከሁሉም ወገን (ምዕራብም ሆነ ምሥራቅ) ድጋፍ እያስገኘላት ነው። ቀድሞ በራቸውን ዘግተውባት የነበሩት እንደ የዓለምገንዘብ ድርጅት ያሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢኮኖሚ ሪፎርሟንየደገፉ ናቸው።

እነዚህን መሠረታዊ መርሖዎች እና ስኬቶች ይዘው ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ለቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔ ደቡብ አፍሪካ የተገኙት።

በጉባዔው ላይ አፍሪካ በልማት እና በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ ተገቢውን ትኩረት እንድታገኝ እንዲሁም በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ አፍሪካዊ መፍትሔዎች እንዲደገፉ የኢትዮጵያን ስኬቶች ምሳሌ አድርገው አቅርበዋል።

ጎን ለጎንም ከአውሮፓ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ መሪዎች እንዲሁም ከታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር ስኬታማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #EBCdotstream #AbiyAhmedAli #G20 #bilateral #multilateral