Search

የመረጃ ማዕከሉን ሰርቨሮች በውኃ የሚያቀዘቅዘው ማይክሮሶፍት ካምፓኒ

ሰኞ ኅዳር 15, 2018 396

በአሁኑ ወቅት ሀገራትና ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የራሳቸውን የመረጃ ማዕከል (Data Center) ለመገንባት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ለዚህም ዋናው ምክንያት ለዜጎች የሚሰጡ የዲጂታል አገልግሎቶችን (የባንክ፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶችን) ፍጥነትና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ነው። በመሆኑም የመረጃ ማዕከሎች ግንባታ ከቴክኖሎጂ ልማት ባሻገር፣ የሀገራትን ዲጂታል ሉዓላዊነት እና የመወዳደር አቅም ለማረጋገጥ እንደ ቁልፍ መሠረተ ልማት እየታየ ነው።

እነዚህ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ የሚፈስባቸው የመረጃ ማዕከሎች፣ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት 24 ሰዓታት ያለ እረፍት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

በውስጣቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰርቨሮችን የያዙት እነዚህ ማዕከላት፣ ለመንቀሳቀስ እጅግ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልጋቸዋል።

ሰርቨሮቹ በሚሰሩበት ወቅት ከፍተኛ ሙቀት ስለሚፈጥሩ፣ ይህንን ሙቀት ለማስወገድ እና ማሽኖቹን ለማቀዝቀዝ ተጨማሪ እና ከፍተኛ ኃይል የግድ ይላል።

ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የመረጃ ማዕከሎችን ሙቀት ለመቆጣጠር የሚያወጡት የኤሌክትሪክ ኃይል ወጪ እየጨመረ በመምጣቱ፣ የተለያዩ አማራጭ ዘዴዎችን ለመጠቀም ተገደዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል አንዱና ውጤታማው መንገድ የኮምፒውተር መሠረተ ልማታቸውን በባሕር እና በወንዝ ቀዝቃዛ ውኃ ማቀዝቀዝ ነው።

የማይክሮሶፍት የባሕር ውስጥ ሙከራ

የመረጃ ማዕከሎችን ለማቀዝቀዝ ከተሞከሩት ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ሰርቨሮችን በውኃ ውስጥ ማስቀመጥ ነው። እ.አ.አ. 2013 ‘ማይክሮሶፍትኩባንያፕሮጀክት ናቲክ’ (Project Natick) በሚል የጀመረው ሙከራ ለዚህ እንደ ማሳያ ይጠቀሳል።

በዚህ ፕሮጀክት ሰርቨሮቹን በብረት በተሸፈነ ግዙፍ ታንከር ውስጥ በማድረግ፣ በቀጥታ ከባሕር ስር በማስቀመጥ የባሕርን ውኃ ለቅዝቃዜ ለመጠቀም ታቅዶ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ፕሮጀክት ሰርቨሮቹን በማቀዝቀዝ ረገድ ውጤታማ ቢሆንም፣ ለግንባታው የሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ፣ የባሕር ላይ ጥገና ውስብስብነት እና ሌሎች ተግዳሮቶች በሰፊው ወደ ተግባር እንዳይገባ አድርገውታል።

የጉግል የባሕር ውኃ ማቀዝቀዣ ዘዴ

የባሕር ውስጥ ሙከራ በተለየ፣ በአሁኑ ወቅት የመረጃ ማዕከሎችበባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በመገንባት የባሕርን ውኃ እየሳቡ ማቀዝቀዝ ውጤታማ በመሆኑ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

ለዚህም በፊንላንድ ሀሚና ከተማ በባሕር ዳርቻ የተገነባው ግዙፉ የጉግል መረጃ ማዕከል ተጠቃሽ ነው።

ከተለመዱት የመረጃ ማዕከላት በተለየ፣ ይህ የጉግል ማዕከል በሰርቨሮቹ መካከል የሚያልፉ የተጠማዘዙ የብረት ቱቦዎች እና የውኃ ፓምፖች ተገጥመውለታል።

ከባልቲክ ባሕር ጥልቅ ክፍል ጋር የተገናኙት የውኃ መስመሮች፣ ቀዝቃዛውን ውኃ በፓምፕ በመሳብ በሰርቨሮቹ ውስጥ በተዘረጉት ቱቦዎች እንዲዘዋወር ያደርጋሉ።

ቀዝቃዛው ውኃ ሰርቨሮቹን በቀጥታ ሳይነካ፣ ሙቀት በሚያመነጩ ክፍሎች መካከል በተዘረጉ ቱቦዎች በማለፍ ሙቀቱን ተሸክሞ ይወጣል፤ ከዚያም ተመልሶ ወደ ባሕር እንዲፈስ ይደረጋል።

ይህ ዘዴ ሰርቨሮቹን ለማቀዝቀዝ ያስፈልግ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወጪ ከመቀነስም ባሻገር፣ በአስተማማኝ መልኩ ሙቀትን ለማስወገድ አስችሏል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ የሚገኙ ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም፣ ሰርቨሮቻቸውን ለማቀዝቀዝ መረጃ ማዕከሎቻቸውን በውኃ አካላት አካባቢ በመገንባት ይህንኑ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ላይ ይገኛሉ።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ