በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቧን እና የራሷን ብሎም የአፍሪካን ድምፅ ማሰማቷን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
ቢልለኔ ስዩም በቡድን 20 የመሪዎች ጉባዔን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በሀገራዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ውይይቶችን ማድረጓን ተናግረዋል።
በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች ጋር በጎንዮሽ መምከራቸውን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት እያመጣች ያለው ለውጥ ለአፍሪካም ምሳሌ የሚሆን እንደሆነ መነሳቱን ገልጸዋል። በተጨማሪም የአፍሪካ ሀገራት የጋራ አጀንዳ እንዲኖራቸው በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከበርካታ ሀገራት መሪዎች ጋርም ውጤታማ ውይይቶችን ማድረጋቸውን አንስተዋል። በተጨማሪ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር፣ ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት እንዲሁም ከተለያዩ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ተቋማት መሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ቢልለኔ ስዩም ጠቅሰዋል።
ከእነዚህ ተቋማት ጋር በተደረገው ሰፊ ውይይት፣ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ያላት ተቀባይነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከፍ እያለ መምጣቱን የሚያረጋግጡ እና በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ምክክሮች ተደርገዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎች ያመጡትን ለውጥ በማስተዋወቅ፣ በኢንቨስትመንት ረገድ የበለጠ የተሳሰረ ግንኙነት ለመፍጠርና ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ውይይቶች ተደርገዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ እና በቀጣይ የምታስተናግደውን 32ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) በተመለከተም ውይይት መካሄዱንም ገልጸዋል።
አፍሪካ እንደ አህጉር እያመጣችው ያለውን ለውጥ የገለጹት ኃላፊዋ፣ ይህንን ለማጉላት እንደዚህ ያሉ መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸውን አንስተዋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በጉባኤው ስኬታማ ተሳትፎ ማድረጓን እና ተጨባጭ ውጤት ማግኘቷን አስታውቀዋል።
በሜሮን ንብረት