Search

አርኪኦሎጂስቶች ያገኙት ውድ ቅርስ

ማክሰኞ ኅዳር 16, 2018 82

አርኪኦሎጂስቶች በኮሎምቢያ የባሕር ዳርቻ ከሰመጠችው እና ‘ቅዱስ ጽዋ’ ተብላ ከተሰየመችው መርከብ የመጀመሪያ የቅርስ ዕቃዎችን አገኙ፡፡
በኮሎምቢያ የሚገኙ አርኪኦሎጂስቶች፣ በውስጧ ባለው ከፍተኛ የሀብት መጠን የተነሳ “ከሰመጡ መርከቦች ቅዱስ ጽዋ” በመባል የምትታወቀው የጥንቷ መርከብ ሳን ሆሴ የመጀመሪያዎቹን ቅርሶች አግኝተዋል።
በፈረንጆቺ 1708 ዓ.ም የብሪቲሽ መርከቦች በሰነዘሩት ጥቃት በካሪቢያን ባሕር የሰመጠችው ይህች መርከብ፣ በ2015 ከተገኘችበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ምርመራ እና ዓለም አቀፍ ውዝግብ ሲያስከትል ቆይቷል።
የመርከቧ ስብርባሪዎች ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ የወርቅና የብር ሳንቲሞች፣ እንዲሁም ኤመራልዶች እና ሌሎች ውድ ዕቃዎችን እንደያዘች ይታመናል። ሀብቷም 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ ፎክስ ኒውስ ዘግቧል።
ሳን ሆሴ ወደ ስፔን ንጉሥ ፊሊፕ አምስተኛ በሚያደርገው ጉዞ ላይ መርከቧ በጌጣጌጥ እና በወርቅ ሳንቲሞች የተሞሉ ሣጥኖችን ጭና እየተጓዘች ነበር።
ሐሙስ ዕለት የኮሎምቢያ የባህል ሚኒስቴር፣ አርኪኦሎጂስቶች ከአካባቢው አንድ የሸክላ ስኒ፣ ሦስት ሳንቲሞች እና አንድ መድፍ ማግኘታቸውን አስታውቋል።
መንግሥት ባወጣው ፎቶግራፎች ላይ ፕሬዚዳንት ጉስታቮ ፔትሮ በተቀበረበት ሥፍራ ተቆፍሮ በተጠበቀ ሁኔታ በተገኘው የነሐስ መድፍ ሲደነቁ ይታያል።
አሁን ይፋ የተደረጉት ቅርሶች ከ300 ዓመታት በፊት መርከቧ ስትሰጥም ከያዘቻቸው ነገሮች ውስጥ ትንሽ ክፍልፋይ ብቻ ናቸው።
ኮሎምቢያ እና ስፔን ሁለቱም የሀብቱ ባለቤትነት የእኛ ነው የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።
ኮሎምቢያ በ1982 መርከቧን ያገኘነው እኛ ነን ከሚለው የአሜሪካ ባለሀብቶች ቡድን ሲ ሲርች አርማዳ ጋር የግልግል ዳኝነት ክርክር ውስጥ ትገኛለች።
በዋሲሁን ተስፋዬ