ኢንዶኔዥያ ከ17 ሺህ በላይ ደሴቶችን፣ 1 ሺህ 300 ብሔረሰቦችን እና 650 ገደማ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን በአንድ ብሔራዊ ማንነት ሥር የተዋሃዱባት ሀገር ነች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፖፑሌሽን ፈንድ በ2025 ባወጣው መረጃ መሰረት የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር 285 ሚሊዮን ገደማ ነው፡፡
ሀገሪቷ በአንድ ወቅት ልትጠፋ ከደረሰችበት የብዝሃነት አያያዝ ችግር ወጥታ ዛሬ ደግሞ ብዝኃነቷን የምታስተዳድርበት የፖለቲካዊ ፍልስፍና ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ጠቃሚ ትምህርቶች የሚገኙበት ነው።

ኢንዶኔዥያ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቷ በርካታ ፈተናዎች እየገጠሟት የመጣች ብትሆንም በሂደቱ ግን ብዝኃነቷ እንዴት ሀብት ማድግ እንምትችል በተግባር ያሳየች ሀገር ነች፡፡
አሜሪካዊቷ አንትሮፖሎጂስት ሎሬይን አራጎን ኢንዶኔዥያን የገለጹት፣ "ዩናይትድ ስቴትስ ብዝኃነት ምን እንደሆነ፣ ምን መሆን እንዳለበት እና ተፈላጊ ግብ ስለመሆኑ ስትከራከር፣ ኢንዶኔዥያ ብዝኃ ማንነትን እና አንድነትን ብሔራዊ ራዕይ አድርጋ በመቅረጽ እና ተግባራዊ በማድረግ ረጅም መንገድ ተጉዛለች" በማለት ነበር።
ፓንቻሲላ (አምስቱ መርሆዎች) የኢንዶኔዥያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ፍልስፍናዊ መሰረት እና የመንግሥት ርዕዮተ ዓለም ነው። ፓንቻሲላ የተለያዩ ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች እና ባህሎች ያሏት ኢንዶኔዥያ ልዩነቶችን አቻችላ የሀገሪቱን አንድነት ለማጠናከር የተነደፉ እና ሀገሪቱ የተገነባችባቸው አምስት የማይነጣጠሉ እና እርስ በርስ የሚጣጣሙ መርሆችን የያዘ ነው።
እነዚህ አምስቱ መርሆዎችም በአንድ አምላክ ማመን፣ ፍትሃዊ እና የሰለጠነ ማንነት፣ የኢንዶኔዥያ አንድነት፣ የጋራ መግባባት ዲሞክራሲ እና ማኅበራዊ ፍትህ ለሁሉም የኢንዶኔዥያ ህዝብ የሚሉት ናቸው፡፡
በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው ይህ ብሔራዊ ፍልስፍና የሁሉም ዜጎች የጋራ መድረክ ሆኖ ያገለግላል። እነዚህ ሀገር-በቀል የሆኑ መሰረታዊ እሴቶች ከምንም በላይ ሚያግባቡ እና ብዝኃ ማንነቶችን አቻችለው ሀገሪቱን በአንድነት ጠብቀው ያቆዩ ናቸው።
ሀገሪቱ ውስጥ ስድስት ዋና ዋና ሃይማኖቶች ማለትም እስልምና፣ ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ፣ ሂንዱይዝም፣ ቡድሂዝም እና ኮንፊሺያኒዝም ሕገ መንግሥታዊ እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፣ ነባር ሀገር በቀል እምነቶችም የሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል። መንግሥት ለእነዚህ እምነቶች ጥበቃ ያደርጋል፤ እርስ በርሳቸው መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው መድረክ ያመቻቻል፤ ከዚያ አልፎ ግን በምንም ሁኔታ ጣልቃ አይገባባቸውም፡፡
240 ሚሊዮን ሕዝበ ሙስሊም በመያዝ በዓለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ ከፍተኛው የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚገኙበት ሀገር ብትሆንም መንግሥቷ ግን ሁሉን አካታች መንግሥት ነው፡፡
ኢንዶኔዥያ የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር አላት፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ተግባራትም በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ማበረታታት፣ የእምነት ውይይቶችን በማደራጀት እና ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሃይማኖቶች ስምምነት መድረኮችን (FKUB) በማቋቋም ነው።
የየአካባቢው ማኅበረሰቦች ማኅበራዊ ስምምነቶችን ለማሳደግ እና በማንነት ላይ የተመሰረቱ ግጭቶችን ለመፍታት እንደ ጎቶንግ ሮዮንግ (የጋራ ትብብር) እና የአካባቢ ተቋማት ባሉ ባህላዊ እሴቶችን ይጠቀማሉ። እነዚህ የማኅበረሰቡን እሴቶች መሰረት ያደረጉ ልምምዶች የመንግሥት ፖሊሲ ብቻውን ሊፈጥር የማይችለውን የመተማመን እና የጋራ መሰረት ይጥላሉ።
ኢንዶኔዥያ እንዴት ብዝኃ ማንነቷን የጠበቀ ሥርዓት መመሥረት ቻለች?
“ፓንቻሲላ” ጽንሰ ሀሳብ የተጀመረው ኢንዶኔዥ ለ500 ዓመታት በፖርቱጋል፣ በፈረንሳይ፣ በጃፓን እና በኔዘርላንድስ ስትገዛ ከነበረችበት ቅኝ ግዛት ነጻ በማውጣት ከ1945 እስከ 1967 በመሯት ሱካርኖ ዘመን ነበር፡፡ ከሀገሪቱ ነጻነት አባቶች አንዱ የሆኑት እና የመጀመሪያው የሱካርኖ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መሐመድ ሃታ አካታች ማኅበረሰብን የመፍጠር ሂደቱን ጽንሰ ሀሳብ ወደ ተግባር የቀየሩ መሪ ናቸው፡፡
ከ1967 እስከ 1998 ሀገሪቱን በወታደራዊ ኃይል የመሩት ሱሃርቶ ግን የሃይማኖት እና ብሔር ጉዳዮች ላይ በግልጽ መወያየትን የሚከለክል ሕግ ተግባራዊ አደረጉ። የሱሃርቶ አመራር ብዝኃ ማንነቷን ከግምት ያላስገባ ስለነበር የእርሳቸው መንግሥት ካለፈ በኋላ ሀገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገባች።
ከ1998 በኋላ የነበረው ጊዜ ‘ሪፎርማሲ’ (ተሐድሶ) ጊዜ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ለረጅም ጊዜ ታፍነው የቆዩ የብሔር እና የሃይማኖት ውጥረቶች የሚፈቱ መሰረታዊ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን መተግበር የተጀመረበት ወቅት ነበር።
ያልተማከለ አስተዳደር እንዲመሰረት የተደረገበት ሲሆን፣ በሀገሪቱ ለሚገኙ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሥልጣን ባለቤት በማድረግ የኢንዶኔዥያ ሪፐብሊክን ከመበታተን ታድጎ እንዲሰባሰብ ለማድረግ ተችሏል።

በ1999 የመጀመሪያውን ነፃ እና ፍትሃዊ የብዝኃ-ፓርቲ አጠቃላይ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ያካሄደች ሲሆን፣ በ2004 ወደ ቀጥታ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተሸጋግራለች። በሀገር አቀፍ እና በአካባቢ ደረጃ የተደረገው ቀጥተኛ ምርጫም ዜጎች በጎሳም ሆነ በማኅበራዊ ደረጃ ሳይለያዩ የሚበጇቸውን መሪዎቻቸውን በቀጥታ እንዲመርጡ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን አስችሏቸዋል።
ሀገሪቱ ያካሄደችው ተሐድሶ በማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ ብሔር ወይም ሃይማኖት ብቸኛ አጀንዳ እንዳይሆኑ ያስቻለ ሲሆን፣ በሁሉም መስፈርት አካታች የሕዝብ ፍላጎትን ማዕከል ያደረገ እና ጽንፈኝነትን ያስወገደ ሥርዓት እንዲሰፍን አስችሏል።
ሀገሪቱ ዛሬ ብዝኃ ማንነቷን ጌጥ እና ሀብት አድርጋ በርካቶች ልምድ የሚቀስሙባት እና ተመራማሪዎች ዕውቀት የሚሰንዱባት ሀገር ሆናለች፡፡ በደቡብ ምሥራቅ እስያ እና በኦሺኒያ ውስጥ የሚገኙ 17 ሺህ 500 ደሴቶች ባለቤት የሆነችው ኢንዶኔዢያ ከፍተኛ-መካከለኛ (upper-middle) ኢኮኖሚን በመገንባት የዓለም 17ኛውን ኢኮኖሚ በላቤት በመሆን የቡድን 20 (G20) አባል ሆናለች።
በለሚ ታደሰ