በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ40 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በዓመቱ የሥራ አፈጻጸም ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ በ2017 በጀት ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከታቀደው በላይ መፈፀሙን ገልጸዋል።
በዓመቱ 34 ሺህ 255 የሚጠጋ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ከ40 ሺህ 904 በላይ ቶን ማቅረብ መቻሉን አስታውቀዋል።
የቡና አምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩን የቡና ማሣ መረጃ በዘመናዊ መንገድ መዝግቦ የይዞታ ማረጋገጫ በመስጠት ለዘርፉ ውጤታማነት እገዛ እያደረገ መሆኑም አንስተዋል።
በክልሉ በ2016/17 ምርት ዘመን የቡና ማሣ ምርታማነት ማሻሻያዎችን በማከናወን የቡና ምርታማነትን በአማካኝ በሄክታር 8.26 ኩንታል ማድረስ እንደተቻለ ተጠቁሟል፡፡
በተለየ ሁኔታ በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ የቡና ምርታማነት መጠኑ በአማካይ 18 ኩንታል መድረሱንም አስረድተዋል።
ክልሉ የይርጋጨፌ ጣፋጭ ቡናን ጨምሮ የተለያ ዓይነት ያላቸውን የቡና ምርቶችን ለማዕከላዊ ገበያ በብዛት በማቅረብ ላይ መሆኑም ተገልጿል።
በተመስገን ተስፋዬ