የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ በኬንያ እና በኡጋንዳ መካከል የሕንድ ውቅያኖስ መዳረሻ ላይ ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ስጋት ውድቅ አድርገዋል።
በቅርቡ ባሕር በርን አስመልክተው ሀሳብ የሰጡት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙዜቬኒ፣ ሀገራቸው ለ100 ዓመታት በጎረቤት ሀገር ወደብ ላይ ጥገኛ ሆና መቆየቷ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ጥገኝነት የቀጣናውን ሰላም ሊያናጋ የሚችል አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸው ነበር።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ኡጋንዳ ከዚህ ችግር ለመውጣት የራሷን የህንድ ውቅያኖስ መዳረሻ የባሕር በር ማግኘት ግድ እንደሆነ እና በኬንያ በኩል በጎ ምላሽ እንደሚጠብቁ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በትላንትናው ዕለት ከኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ጋር የተገናኙት ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ፤ ጉዳዩ በአፍሪካዊ ውንድማማችነት መፍትሔ የሚያገኝ መሆኑን በመግለጽ በጎ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በኡጋንዳ የባሕር በር ጥያቄ ምክንያት በሁለቱ ሀገራት መካከል ግጭት ይነሳል ብለው የሚያወሩ ወገኖች ሀሳብ እንደማይሳካ እና እነዚህ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ፕሬዚዳንት ሩቶ አሳስበዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሩቶ በኡጋንዳ ቶሮሮ ለሚገነባው ዴቭኪ ግዙፍ የብረታ ብረት ፋብሪካ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ዩጋንዳ በኬንያ በኩል ወደ ሕንድ ውቅያኖስ መዳረሻ የባሕር በር እንድታገኝ ግጭት አያስፈልግም ብለዋል፡፡
ሀገራቱ በንግድ እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው እና ሀገራቸው ይህን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗንም ቃል በመግባት አረጋግጠዋል።
"ኡጋንዳ እና ኬንያ እህትማማቾች ስለሆኑ ለትብብር እንጂ ለአሉታዊ ውዝግቦች ጊዜ የላቸውም" ያሉት ፕሬዚዳንት ሩቶ፣ ኡጋንዳ በኬንያ በኩል የባሕር በር እንድታገኝ ሀገራቸው ፈቃደኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ኬንያ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ብቻ ሳይሆን መንገድ እና የባቡር ሀዲድን ለማስፋፋት በስፋት እየሠራች ያለችው ቀጣናው አንድ ሆኖ አብሮ መልማት እንዳለበት ስለምታምን መሆኑንም ገልጸዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት በናይሮቢ አቅራቢያ ከምትገኘው የሞምባሳ ወደብ መዳረሻ ሪሮኒ ተነስቶ ኡጋንዳን እና ኬንያን እስከሚያዋስነው ማላባ የሚደርሰውን መንገድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት እንደሚያስጀመሩ ተናግረዋል።
የፈጣን መንገድ ማስፋፊያው ወደ ሞምባሳ ወደብ የሚደረገውን ጉዞ በጣም ፈጣን እና ቀላል እንደሚያደርገው ጠቁመው፣ ይህ ለሁለቱ ሀገራት ስልታዊ ትስስር አስፈላጊ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በኬንያ እና ዩጋንዳ መካከል ያለውን የነዳጅ ቧንቧ መሥመር እና ሁለቱን ሀገራትን የሚያስተሳስሩ ሌሎች መሰረተ ልማቶች በመንግሥት እና ግል ትብብር እንዲስፋፉ ለሚኒስትሮቻቸው መመሪያ መስጠታቸውንም አስታውሰዋል።
ሁለቱ እህትማማች ሀገራት በትብብር አብረው ማደግ የሚችሉባቸው ሰፋፊ ዕድሎች መኖራቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ሩቶ፣ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ትብብሩን ማላቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
እስከ ኮንጎ ድንበር ድረስ ያለውን መሰረተ ልማት ጭምር በጋራ ለመሥራት እና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እና የአፍሪካ አህጉርን የትብብር እና አንድነት ለማጠናከር እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል።

"ዛሬ እያደረግን ያለነው ፕሮጀክት ማስጀመር ብቻ አይደለም፤ የአፍሪካ የነጻነት ሂደት አካል ነው፤ ሂደቱ ደግሞ ቀጣይ ነው" ያሉት ደግሞ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሱቬኒ ናቸው።
ወደብ አልባ የሆነችው ኡጋንዳ ከህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ያላት ርቀት ወደ 743 ኪሎ ሜትር ገደማ ሲሆን፣ ባሕሩን ለማግኘት ኬንያን ማቋረጥ ይጠበቅባታል።
ሁለቱ መሪዎች በጋራ ያስጀመሩት እና በምሥራቅ ኡጋንዳዋ የአስተዳድ እና ንግድ ከተማ ቶሮሮ ከተማ የሚገነባው የብረታ ብረት ፋብሪካ በ500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚሠራ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ.ከ2027 ጀምሮ በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን ብረት ማምረት እንደሚጀመር ኬንያን ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (KBC) መረጃ ያመላከክታል።
በለሚ ታደሰ