ከ6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባትና በስፋቷ ከአዲስ አበባ ጋር ተቀራራቢ የሆነችው ሲንጋፖር፣ ከ90 በመቶ በላይ የምግብ ፍጆታዋን ከውጭ ሀገራት ታስመጣለች።
ለዚህ ዋናው ምክንያት የሀገሪቱ የቆዳ ስፋት እጅግ ያነሰ መሆኑ ሲሆን፣ ካላት ውስን መሬት ውስጥ አብዛኛው ለመኖሪያና ለኢንዱስትሪ ግንባታ በመዋሉ ለእርሻ የሚተርፍ ቦታ የላትም።
በዚህም ምክንያት በሲንጋፖር ለእርሻ የሚውለው የመሬት ስፋት ከጠቅላላ የሀገሪቱ ስፋት ከአንድ በመቶ በታች ነው።
ሆኖም ሲንጋፖር ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር '30 በ 30' (30 by 30) የሚል ስያሜ ያለው እቅድ ቀርጻ ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው።
በዚህ እቅድ መሰረት ሀገሪቱ የግብርና ሥራዋን ለማዘመን የሚረዳ የ"ማማ ላይ እርሻ" (Vertical Farming) መጠቀም ጀምራለች። በጥቂት ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ብዙ ምርት ለማግኘት በሚያስችለው በዚህ የከፍታ ግብርና ሥራም ውጤታማ መሆን ችላለች።
‘ስካይ ግሪንስ’ (Sky Greens) በተባለውና በመሰል ኩባንያዎች አማካኝነት መልማት የጀመረው ይህ የእርሻ ሥርዓት፣ አትክልቶች የሚዘሩት በመሬት ላይ ሳይሆን እስከ 9 ሜትር ቁመት ባላቸው ቀጥ ያሉ የአሉሚኒየም መደርደሪያዎች ላይ ነው።
ይህ እቅድ እ.አ.አ. በ2030 ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ የሀገሪቱን የምግብ ፍጆታ በሀገር ውስጥ ለማምረት ያለመ ነው። ይህም ከአንድ በመቶ በታች በሆነው ለግብርና በተከለለ መሬት ላይ የሚተገበር ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
የቦታ ውስንነት ከመልማት ያላገዳት ይህች ሀገር፣ የሕዝቧን የምግብ ፍላጎት ለመሸፈን ይህን መሰል ዘመናዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ እየሆነች ትገኛለች።

የሲንጋፖር የትናንት ታሪክ ምን ይመስል ነበር?
ዛሬ ላይ በዓለማችን ካሉት የበለፀጉ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሲንጋፖር፣ እዚህ ደረጃ ከመድረሷ በፊት አስከፊ የሚባሉ የድህነት ታሪኮችን አሳልፋለች።
ታሪኩ ከመቀየሩ ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ እጅግ ዝቅተኛ ነበር። በሌላ በኩል ውስን የሆነው መሬቷ ብዙ ሕዝብ ለመመገብ ባለመቻሉ በምግብ እጥረት ትፈተን ነበር።
በእነዚህና መሰል ችግሮች በድህነት አዘቅት ውስጥ የነበረችው ይህች ሀገር አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ተነሳች። የዘመናዊቷ ሲንጋፖር መስራች አባት ተብለው በሚታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዋን ዩ (Lee Kuan Yew) አማካኝነት በተቀረፀ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የድህነት ታሪኳን ሰርዛ የሕዝቧን የሚያኮራ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ በሙሉ ልብና ቁርጠኝነት መጓዝ ጀመረች።

ከዓመታት በኋላም የሲንጋፖር ታሪክ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ በዓለማችን ጠንካራ ኢኮኖሚ ካላቸው ሃብታም ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች።
ሲንጋፖር በኢንዱስትሪ አድጋ የሕዝቧ የኑሮ ሁኔታ ተቀይሯል። ውስን የሆነው የመሬት ሀብቷ በእርሻና ግብርና መስክ በስፋት እንዳትሰማራ ቢያደርጋትም፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በምግብ ምርት ራስን ለመቻል እያደረገች ያለው ጥረት ለዓለም አስተማሪ ሆኗል።
በዋሲሁን ተስፋዬ