በፖለቲካ ልዩነት ነፍጥ ያነገቡ ወገኖች ሰላማዊ የውይይት አማራጭን እንዲከተሉ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቅርቧል።
4ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ በሐረር ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደተናገሩት፤ በጠብመንጃ መፍትሄ መፈለግ ጥፋትን አስከትሏል።
የታላቅነት መለኪያ የደከመውን ማገዝ፤ የወደቀውን ማንሳት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ፀሐፊው፣ የአንድነት አረም የሆነውን ጥላቻ በመንቀል ሰላምን መትከል ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልል አሁንም መፍትሄን በትጥቅ ትግል የሚፈልጉ ወገኖች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስም ጥሪ አቅርበዋል።
የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ዑመር በበኩላቸው ሰላም ለሕዝቦች ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፣ ይህንን በአግባቡ መያዝ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ኬይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የሃይማኖት ተቋማት በሰላም እና በሀገር ግንባታ ቁልፍ ሚናን የሚጫወቱ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሰላምን ለማፅናት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ኮንፍረንሱ "ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ ለተከታታይ ሁለት ቀናት በሐረር እየተካሄደ ይገኛል።
በቴዎድሮስ ታደሰ