ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ለከፍተኛ ግብር ከፋዮች በልዩ ሁኔታ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንዲሰጥ መመሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት፣ የመጀመሪያውን የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ እና የናሽናል ሲሚንቶ ሆልዲንግ ሼር ካምፓኒ የቦርድ ሊቀመንበር ለሆኑት ለአቶ ብዙአየሁ ታደለ ማስረከቡን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታውቋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ፤ ለአልሚዎች እና ለከፍተኛ ግብር ከፋዮች ይህንን ክብር መስጠት መቻሉ የተቋሙ የሪፎርም ሥራ አካል ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፤ በሀገር ላይ ለውጥ በማምጣት ለብልፅግና አጋዥ የሆኑ ሥራዎችን እየሠሩ የሚገኙ ዜጎች፣ የሀገርን ክብር እና የሠሩትን ተግባር የሚመጥን አገልግሎት ማግኘት እንደሚገባቸውም አስረድተዋል።
በተጨማሪም ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለአምባሳደሮች፣ ለሀገር ባለውለታዎች እና ለከፍተኛ ግብር ከፋዮች የተፋጠነና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥበት ልዩ የመገልገያ ቦታ መዘጋጀቱንም ወይዘሮ ሰላማዊት አስታውቀዋል።