የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በ7ኛው የአፍሪካ እና አውሮፓ ህብረት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ ጥሪ አቅርበዋል።
ዋና ጸሐፊው ይህ እርምጃ ጥልቅ ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት የሚቀለበስበት መንገድ መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡
የአፍሪካ እና አውሮፓ ሀገራት በተባበሩት መንግስታት 40 በመቶ ያህሉን የሚወክሉ በመሆናቸው የአዲሱ ዓለም ማዕከላዊ ምሰሶ የመሆን አቅም እንዳላቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያ፣ የአየር ንብረት እና የሰላም ጉዳይ ሁለቱ ህብረቶች በትብብር የሚሰሩባቸው ወሳኝ ዘርፎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አሁን ያለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ መዋቅር ፍትሃዊና ውጤታማ አይደለም በማለት የተቹት ዋና ፀሀፊው፤ የአፍሪካን የዕዳ ማቆም፣ የአበዳሪነት አቅምን በሦስት እጥፍ ማሳደግ እና የአፍሪካ አገራት በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የተሻለ ተሳትፎና ተጽዕኖ እንዲኖራቸው መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
አፍሪካ በንፁህ ኃይል እና በወሳኝ ማዕድናት የበለጸገች በመሆኗ፣ ይህ ሀብት ወደ ከፍተኛ እሴት ወደ ሚጨምር ምርት እንዲቀየር ጠይቀዋል።
ዋና ጸሐፊው በዩክሬንና በጋዛ ያለው ጦርነት “የሰው ልጅ ትልቅ ውድቀት” መሆኑን በመግለፅ፤ በዓለም ዙሪያ ያለው ደም መፋሰስ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
አንቶኒዮ ጉተሬ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፤ የአፍሪካ ህብረት እና አውሮፓ ህብረት ግንኙነት ዓለምን የተረጋጋች፣ ሁሉን አቀፍ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት ለማድረግ እውነተኛ ኃይል አለው ሲሉም አበረታተዋል።
በሙሀመድ አልቃድር
#Ebc #Ebcdotstream #AfricanUnion #EuropeanUnion #AUEU25