Search

የባሕር በር ስለሌለው ወደኋላ ሊተው የሚገባ ሀገር መኖር የለበትም፡- የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየሦስት ዓመቱ ወደብ የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ጉባዔን ያደርጋል።

ዘንድሮም ሦስተኛው ወደብ የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ጉባዔ በቱርክሜኒስታን አዋዛ ከተማ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

ጉባዔው በተጀመረበት ወቅት የተባበሩትመንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባደረጉት ንግግር፥ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የሚደርስባቸው ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን አንስተዋል።

ይህ ችግር በጋራ መቀረፍ እንዳለበት ያነሱት ዋና ጸሐፊው፤የባሕር በር ያላቸው ሀገራት የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት በትብብር መስራት አለባቸው፤ የባሕር በር ስለሌለው ወደኋላ ሊተው የሚገባ ሀገር መኖርም የለበትምብለዋል።

ሦስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደብ የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ኮንፈረንስ፥ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማትን ለማፋጠን ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን ለማስተዋወቅ ያለመ ነው።

በዓለማችን 44 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ሲኖሩ ከነዚህ መካከል 32 ያህሉ ታዳጊ ሀገራት ናቸው። 

እነዚህ ታዳጊ የባሕር በር አልባ ሀገራት 500 ሚሊዮን ነዋሪ ይዘው፤ ከፍተኛ ለሆነ የትራንስፖርት ወጪ፣ ለውስን ገበያ ተደራሽነት እና ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተጋላጭ ሆነው ይገኛሉ። 

ከነዚህ 500 ሚሊዮን ያህል ሕዝቦች መካከል 25 በመቶ ገደማ ወይም 120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብን ይዛ የምትገኘው ኢትዮጵያም የመሰል ተግዳሮቶች ተጋፋጭ ናት።

በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አካቶ በጉባዔው ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛል። 

ኢቢሲ ዶትስትሪም ያነጋገራቸው የልዑኩ አባል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (/) ዛሬ ከተጀመረው ጉባዔ አስቀድሞ በትናንትናው ዕለት የፓናል ውይይት መደረጉን ገልጸዋል። 

በፓናል ውይይቱ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍም፤ ኢትዮጵያ ባልተገባ መንገድ የባሕር በር በማጣቷ የደረሰባትን ኢኮኖሚያዊ ጫና እና ሌሎችንም ተግዳሮቶች ለተሳታፊዎች ማስገንዘባቸውን ጠቁመዋል። 

ታዳጊ ሀገራት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በሚያደርጉት የተለያዩ የዕድገት ውጥኖች አለመሳካት፤ ቀጥተኛ የባሕር በር ማጣት ትልቅ ሚና ያለው እንደሆነ በፓናል ውይይቶቹ መነሳቱንጠቁመዋል። 

ይህን ለማስተካከል የሕግ አውጭው ወይም የየሀገራቱ ምክር ቤት፥ ከወደብ እና ወደብ ልማት ጋር በተያያዘ እንዲሁም አማራጭ መሰረተ ልማቶችን ከማሟላት አኳያ ለውጦች እንዲመጡመስራት እንዳለበት ተነስቷልም ነው ያሉት።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እና ንግዷን በማጠናከር የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከጫፍ መድረሷንም ነው የተናገሩት። 

ሀገሪቱ በበርካታ መንገድ ውጤታማ ሥራዎችን ብትከውንም፣ የባሕር በር ማጣት በርካታ የውጭ ምንዛሬዋን በባሕር በር ኪራይ ላይ ፈሰስ እንድታደርግ መገደዷ የሚፈለገው የለውጥ ደረጃ እንዳትደርስ የሚጎትት ምክንያት መሆኑንም አንስተናል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የአንድ ሀገር ህልውና ከሚመሰረትባቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑ ተሰምሮበታልም ብለው፤ ይህ በተለይ ለታዳጊ ሀገሮች እጅግ አስፈላጊ መሆኑም እንደተነሳ ገልጸዋል።

ዛሬ ዋናው ጉባዔ በተጀመረበት ወቅትም አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባደረጉት ንግግር፥ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የሚደርስባቸው ተጽእኖ ከባድ መሆኑን አንስተዋል። 

ይህ ችግር በጋራ መቀረፍ እንዳለበትያነሱት ዋና ጸሐፊው፤የባሕር በር ያላቸው ሀገራት የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት በትብብር መስራት አለባቸው፤ የባሕር በር ስለሌለው ወደኋላ ሊተው የሚገባ ሀገር መኖርም የለበትምብለዋል።

ጉባዔው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 4 ቀናትእንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፤ በበርካታ ጉዳዮች ላይ እንደሚመከርበት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ልዑክም ከጉባኤ ተሳትፎው ጎን ለጎን የተለያዩ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ውይይቶችን እንደሚያካሂድ ይጠበቃል።

በሰለሞን ከበደ