Search

ብዙዎች ሊያዩት የሚሹት የ''ሀይሊ ጉቢ'' የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ

ረቡዕ ኅዳር 17, 2018 131

ከቀናት በፊት በአፋር ክልል አፍዴራ ወረዳ በሚገኘው ''ሀይሊ ጉቢ'' ተራራ ላይ የተከሰተው አዲሱ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ከመሬት 40 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ የደረሰ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የሴስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ አየለ አስረድተዋል፡፡

እሳተ ገሞራ ከ10ሺህ እስከ 12ሺህ ዓመታት ባለ ጊዜ ካልፈነዳ ‘እንቅስቃሴ የሌለው’ እሳተ ገሞራ ከሚባለው ተርታ እንደሚመደብ ጠቁመው፤ ''ሀይሊ ጉቢ'' ከዚህ እንደማይመደብ ገልፀዋል፡፡  

ፕሮፌሰር አታላይ በተጠቀሱት ዓመታት ፍንዳታ ተከስቶ እንደነበር አሊያም እንዳልነበር ለመለየት የሚያስችል ተጨባች መረጃ እንደሌለም ለኢቢሲዶትስትሪም አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 በላይ ንቁ እሳተ ገሞራዎች (Active volcano) ስለመኖራቸው ገልፀው፤ ''ሀይሊ ጉቢ'' ከነዚያ መካከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም የእሳተ ገሞራ መጠን በሚለቀው የጋዝ መጠን እና ብናኝ እንደሚለካ ያስረዱት ፕሮፌሰሩ፤ ከመሬት 40 ኪሎሜትር ከፍታ የደረሰው የ''ሀይሊ ጉቢ'' እሳተ ገመራ ፍንዳታ ከፍተኛ የሆነ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ እና ሰልፈርዳይ ኦክሳይድ ስለመልቀቁ አመላክተዋል፡፡

ይህም በ2003 ዓ.ም ተከስቶ ከነበረው እና ከፍተኛ የቅልጥ አለት ከነበረው የነብሮ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ የጠነከረ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

እንዲሁም ''ሀይሊ ጉቢ'' እሳተ ገሞራ ፍንዳታ ለመሬት ቅርብ የነበር በመሆኑ በፈጠረው እርግብግቢት ሳቢያ የመሬት መንቀጥቀጥ አለመከሰቱን ገልፀዋል፡፡ 

ሆኖም ግን የፈጠረው ጭስ በተለይም ከመሬት ወደ ላይ ከፍ በማለቱ ሳቢያ የንፋስ አቅጣጫውን ተከትሎ እየሄደ ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዚያ በኩል ለሚደረጉ በረራዎች አመቺ ባለመሆኑ በረራዎች ሊሰረዙ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

አክለውም በተራራዎቹ ላይ ለትንበያ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን በማኖር ፍንዳታ ሊከሰት ሲል ማወቅ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

በዚህም ሁነቱን በቦታው በመገኘት ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለመመልከት ለሚሹ የሀገር ውስጥ ብሎም የውጪ ጎብኚዎች ሳቢ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

ከክስተቱ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እና ሊፈጠሩ ከሚችሉ ጉዳቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ያሳሰቡት ፕሮፌሰሩ፤ አሁንም ቢሆን ክስተቱ ካለበት ስፍራ በበቂ ርቀት መሆን እና የፊት ጭንብል ማድረግ አግባብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአፎምያ ክበበው

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #Afar #volcano