የባህር በር ጉዳይ ከተረሳበት ወደ አጀንዳነት መጥቷል፡፡ ወደ ኋላ ሦስት አስርት ዓመታትን ብንመለስ፣ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እና ጥያቄ ማንሳት እንደ አላዋቂ የሚያስቆጥር ነበር፡፡
በ1980ዎቹ ኢትዮጵያ ከባሕር በር ስትገፋ፣ የሚመጣውን ቀውስ መተንበይ የሚችሉ ዜጎች ታጥተው ሳይሆን ለጉዳዩ ትኩረት የሚሰጥ ቁርጠኛ አመራር ባለመኖሩ ነው ይላሉ ጉዳዩን የተከታተሉ ምሁራን።
እንዲያውም ሁኔታው ያሰጋቸው ምሁራን የባሕር በር አማራጭ ማጣት የሚያስከትለውን ጉዳት፣ በተለይም ከዓመታት በኋላ የሚጨምረውን የሕዝብ ቁጥር ታሳቢ በማድረግ ለማስረዳት ሲሞክሩ፣ “ወደብ ሸቀጥ ነው፤ ስንፈልግ እንገዛዋለን” የሚል ምላሽ ይሰጣቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ዛሬ ‘ኢትዮጵያ የበይ ተመልካች መሆኗ ያብቃ’ በሚል እሳቤ የባሕር በር ጉዳይ የህልውና ጥያቄ ሆኗል፡፡
90 በመቶ የሚሆነውን የወጪ እና ገቢ ንግዷን በጅቡቲ ኮሪደር የምታከናውነው ኢትዮጵያ፣ ለወደብ ክፍያ በዓመት ቢሊዮን ዶላሮችን ወጪ ታደርጋለች፡፡
ይህም መጠን በየተወሰነ ዓመት ጊዜ ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብን የመሰለ ፕሮጀክት ለመገንባት የሚያስችል አቅም ነው፡፡
ከኢቲቪ ዳጉ መሰናዶ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ባለሙያው ዓሊ ሁሴን (ዶ/ር) የወደብ ባለቤትነት ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ እና የሥራ አጥነት እንዲቀንስ ያስችላል ይላሉ።
አምራችነት የሀገር እድገት መሠረት ቢሆንም፣ ጥሬ እቃ ለማስገባት እና ያለቀለት ምርት ለመላክ ከፍተኛ ተግዳሮት ስለመኖሩም ነው የተናገሩት።
ከዚህም ባሻገር የውጭ ኢንቨስተሮች ባለው ከፍተኛ የወደብ ክፍያ ምክንያት በይበልጥ ላይሳቡ እንደሚችሉም አስረድተው፤ የወደብ ባለቤትነት ጉዳይ ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ያለ ባህር በር አማራጭ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በተለያዩ ጊዜያት ከ7.5 እስከ 8.5 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ፤ ሀገሪቷ የወደብ ባለቤት ብትሆን ደግሞ በተሻለ ፍጥነት ለማደግ ያስችላል ያሉት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ የሥነ አመራር ባለሙያ የሆኑት ሳሙዔል ጌታቸው (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በዓለም ላይ አብዛኛው የንግድ ልውውጥ በባህር ትራንስፖርት የሚካሄድ ሲሆን፣ የወደብ አማራጭን ማስፋት አንድን ሀገር በኢኮኖሚ ፈር ቀዳጅ እንደሚያደርጋት ከ8 ያላነሱ የለሙ የባህር በር አማራጮች ያሏት ደቡብ አፍሪካ ብቁ ማሳያ መሆኗን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የባህር በር አማራጭ ከማግኘት እስከ ባህር በር ባለቤትነት የዘለቀ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ሲሳይ ደመቁ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነትን በማስከበር፣ የባህር ክልሉን እና በውስጡ ያሉ ሀብቶችን የመጠቀም መብትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በአፎሚያ ክበበው