Search

ሉሲ በኖረችበት ዘመን እንደኖረ የተገመተ የ3.4 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያለው ቅሪተ አካል በኢትዮጵያ ተገኘ

ሓሙስ ኅዳር 18, 2018 50

3.4 ሚሊዮን ዓመት ገደማ ዕድሜ ያለው ቅሪተ አካል በአፋር ክልል መገኘቱን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከተመራማሪዎች ጋር በመሆን ግኝቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፤ ቅሪተ አካሉ የተገኘው በአፋር ክልል “ወረንሰ ሚሌ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑ ተገልጿል።
ግኝቱን ይፋ ያደረጉት በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዮሐንስ ኃይለሥላሴ (ፕ/ር)፣ አዲሱ ግኝት የ3.4 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ እንዳለውና ይህም “ሉሲ” (ድንቅነሽ) በኖረችበት ዘመን ይኖር እንደነበር አመላካች ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ለቅሪተ አካሉ ''የሉሲ የቅርብ ዘመድ'' የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡
 
በአፋር ክልል በተለያዩ የጥናት ጣቢያዎች መሰል ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን የጠቆሙት ተመራማሪው፣ የተገኘው ቅሪተ አካል በሰው ዘር የለውጥ ሒደት (Evolution) ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም ያረጋገጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በበኩላቸው፤ መሰል የምርምር ግኝቶች ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትና የሰው ዘር መገኛ መሆኗን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል፡፡
የሉሲ ወይም የድንቅነሽ ቅሪተ አካል በሕዳር ወር 1967 ዓ.ም. በአፋር ክልል “ሃዳር” በተባለ ቦታ መገኘቱ ይታወሳል፡፡
 
በመሀሪ ዓለሙ