Search

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የልዑል ዊሊያም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

ሓሙስ ኅዳር 18, 2018 36

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ፣ በልዑል ዊሊያም የሚበረከተውን የተስክ (Tusk) የአፍሪካ የዱር እንስሳት ጥበቃ ሽልማትን አሸነፉ።
“TUSK Conservation Award” የተሰኘው ይህ ሽልማት፤ በአፍሪካ የዱር እንስሳት ጥበቃ መስክ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ላበረከቱ መሪዎች የሚሰጥ ክብር ሲሆን፣ የዘንድሮው አሸናፊ አቶ ኩመራ ሽልማታቸውን ትናንት በለንደን ከተማ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ከልዑል ዊሊያም እጅ ተቀብለዋል፡፡
አቶ ኩመራ ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ለዱር እንስሳት እና ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ያበረከተውን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አብራርተዋል።
በቀጣይም በዱር እንስሳት እና በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ላይ በአጋርነት በመሥራት ለዘርፉ የበለጠ ትኩረት እና እንክብካቤ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን ሽልማቱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፤ "አቶ ኩመራ ዋቅጅራ የልዑል ዊሊያም የTUSK Conservation Award የአፍሪካ ተሸላሚ በመሆናቸው ትልቅ ክብር ይሰማኛል" ብለዋል።
የአቶ ኩመራ ዕውቅና ለሦስት አስርት ዓመታት በዘርፉ ላይ በሠሩት ጠንካራ ሥራ የተገኘ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ብሩክ፣ ኤምባሲው በአቶ ኩመራ ስኬት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ገልጸዋል፡፡
 
በለሚ ታደሰ