ሳዑዲ አረቢያ በህንጻ ላይ የገነባችው ግዙፍ ስቴዲየም እየተባለ በረጅም ህንጻ ላይ ስታዲየም እንዴት ሊሰራ ይችላል የሚል ጥያቄ ሲያጭር የነበረ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ብዙ ተመልክተናል። ነገሩ እውነት ሊመስል የማይችል የሆነባቸው ምስሉ ትክክለኛ አለመሆኑን ሲነግሩንም ቆይተዋል።
ይሁንና ከስታዲየሙ በላይ እጅግ የሚደንቅ ግዙፍ እና ሊሆን አይችልም የሚያስብል ከተማ እየገነባች ያለችው ሳዑዲ ምን ስታዲየም ይገርማችኋል? ስታዲየሙን የሚያስንቅ ከተማ እየገነባን ነው እያለች ነው።
ኒኦም በሰው ልጅ ታሪክ ከፍተኛ በጀት የተመደበለት ግዙፍ ፕሮጀክት ሲሆን፣ በሳዑዲ አረቢያ የሰሜን ምዕራብ በረሃ ታቡክ በተባለው ክልል ውስጥ የሚገነባ የወደፊት ከተማ ነው።

አጠቃላይ የግንባታ ወጪው ከአንድ ትሪሊየን ዶላር በላይ እንደሚደርስ የሚገመተው ይህ አዲስ ከተማ በተመደበለት ከፍተኛ በጀት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገሩ ከእውን ይልቅ ወደ ሳይንስ ልቦለድነት የሚጠጋ የዓለማችን ግዙፉ ፕሮጀክት ነው።
ከእነዚህም መካከል በሳዑዲ አረቢያ የሰሜን ምዕራብ በረሃ ጭው ባለ አሸዋ ላይ የሚገነባው የኒኦም ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነው ዘ ላይን የተሰኘው አዲስ ፕሮጀክት ይገኝበታል።

ይህ እጅግ ዘመናዊ ከተማ በእቅዱ መሰረት ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ውጫዊው ክፍል ቁመቱ 500 ሜትር ቁመትና 170 ኪ.ሜትር ርዝመት ባለው ልዩ መስታወት የሚገነባ ሲሆን የከተማው አጠቃላይ ስፋት 200 ሜትር ይሆናል።
ዘ ላይን ከተማ በሺህ የሚቆጠሩ ሊፍቶች የሚኖሩት ሲሆን እነዚህ ሊፍቶች እንደተለመዱት ሊፍቶች ወደላይና ወደታች ብቻ ሳይሆን ወደ ቀኝ ወደ ግራ እና ወደ ተፈለገው አቅጣጫ መጓዝ የሚችሉ ገመድ አልባ ሊፍቶች ናቸው ።
በምሽት ወቅት ከተማዋን ከሚያደምቋት መብራቶች በተጨማሪ ሲመሽ በከተማዋ ላይ ከፍ ብለው የሚሰቀሉ ጨረቃ መሰል LED (ሰው ሰራሽ ጨረቃ) መብራቶች ከተማዋን ያደምቋታል።

አዲስ በሚገነባው የኒኦም ፕሮጀክት በሚገኘው የባህር ዳርቻ ያለው አሸዋ ከተለመደው ተፈጥሯዊ አሸዋ የተለየ ይሆናል። (ይህ በመጀመሪያው እቅድ ላይ የነበረ ሀሳብ ከአካባቢ ጥበቃና ከወጭ አንጻር በተሻሻለው እቅድ ላይ ባይካተትም) በልዩ ኬሚካል ወይም ቴክኖሎጂ ተነክረው እንዲያበሩ ወይም እንዲያብረቀርቁ የሚደረጉ ናቸው። አሸዋው በምሽት የባህር ዳርቻውን በማስዋብ ልዩ ውበት እንዲሰጡ ይደረጋል ተብሏል።
ረጅሙ የላይን ከተማ ከላይኛው ክፍል በተጨማሪ ከመሬት ስር የተገነቡ ሁለት ክፍሎችም እንዲኖሩት ተደርጎ የሚሰራ ነው። በዚህም መሰረት ሕዝብ በሚኖርበት የከተማዋ ላይኛው ክፍል ምንም አይነት መኪናም ሆነ የመኪና መንገድ አይኖርም። ከተማዋ ጠቅላላ ትላልቅ ፓርኮች፣ አረንጓዴ ቦታና የእግረኛ መንገድ ብቻ እንዲኖራት ተደርጋ የምትገነባ ይሆናል።

ከመሬት በታች ያለው ሁለተኛ ክፍል ደግሞ ለኒኦም ከተማ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች የከተማዋን ቆሻሻ የሚያስወግዱ በሮቦት የታገዘ አገልግሎት ሰጭዎች ይገኛሉ።
በሶስተኛውና የመጨረሻው (The Spine) ተብሎ በሚጠራው የምድር ክፍል ደግሞ ከከተማዋ ጫፍ እስከ ጫፍ በ20 ደቂቃ ብቻ የሚያደርስ በሰዓት 500 ኪ.ሜ የሚምዘገዘግ ፈጣን ባቡር በአየር ላይ የሚበሩ ታክሲዎችና ፈጣን ድሮኖች የሚገኙበት ክፍል ነው።
ሌላው በዚህ ከተማ ለመኖር የሚፈልግ ሰው የግሉ ቤት መግዛት አይጠበቅበትም። የመኖሪያ ቤት፣ የምግብ፣ የጤናም ሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ የሚከናወነው ልክ እንደ ኔትፍሌክስ በወርሃዊ ክፍያ ነው።
ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ እስከ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ነዋሪዎችን መያዝ ይችላል በተባለው ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች መታወቂያ ወረቀት ወይም ፓስፖርት መያዝ አያስፈልጋቸውም። መታወቂያ ፓስፖርት የባንክ ካርድ ሁሉ የሚጠቀሙት ፊታቸውን እና ዐይናቸውን በማሳየት ወይም በባዮሜትሪክ ዘዴ ነው።

በኒኦም ሲቲ የሚተከሉት ልዩ ካሜራዎች የከተማዋ መንገዶችና በእያንዳንዱ አማካኝ ስፍራ ወንጀልን በማየት ብቻ መተንበይ የሚችሉ ካሜራዎች ይገጠማሉ። ይህ አይነት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚታገዙ የቁጥጥር ካሜራዎች በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የዓለም ከተሞች ውስጥ አገልግሎት ላይ መዋል ጀምረዋል። በዚህ ከተማ ደግሞ በስፋት እንደሚተገበር ተነግሯል።
እነዚህ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚሰሩ ካሜራዎች ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል እና ጥርጣሬን የሚያጭሩ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት አስቀድመው የከተማዋን ፀጥታ ለሚቆጣጠረው ማዕከል ያሳውቃሉ።
በዚህ 500 ሜትር ቁመት እና 200 ሜትር ስፋት ወዳለው ኒኦም ሲቲ ያለው የሙቀት መጠን ከከተማው የመስታወት ግድግዳ ውጭ ካለው ጋር ፈፅሞ የተለያየ ነው። በውጭው ያለው ሙቀት ከፍተኛ ደረጃ ቢደርስ እንኳን እዚህ ከተማ ውስጥ በAI ቁጥጥር የሚደረግበት የራሱ የሆነ የአየር ንብረት ይኖረዋል።
በዚህ ከተማ ዳር እና ዳር በሚገነቡት በሺህ የሚቆጠሩ ህንጻዎች ላይ የተለያዩ አትክልቶች እና አረንጓዴ ተክሎች እንዲያበቅሉ መደረጉ ለከተማዋ አየር ንብረት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።

ይህ በሁለቱም የከተማዋ ክፍል እንደግድግዳ ቆሞ ኒኦም ሲቲን ከበረሀው የሚለያት ልዩ መስታወት 500 ሜትር ቁመትና 170 ኪ.ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሲሆን ከተማዋን ከአሸዋማው በረሀ ከመለየትም በተጨማሪ ከፀሀይ ብርሀን የሚያገኘውን ሀይል ወደ ኤሌትሪክ ሀይል በመለወጥ ለከተማዋ የሀይል አቅርቦት እንዲያቀርብ ሆኖ የተሰራ ነው።
በተጨማሪም የበረሀው አቧራ እንዳያቆሽሸው ራሱን በራሱ ማፅዳት ይችላል። ይህ ገና ዲዛይኑ ይፋ ከሆነ ጀምሮ በአስደናቂነቱ መነጋገሪያ እየሆነ ያለው የኒኦም ሲቲ ከተማ በአሁኑ ወቅት ግንባታው ተጀምሮ ስራዎች እየተከናወኑ የሚገኝ ሲሆን የግንባታውን መሰረት ለማቆም የአፈር ቁፋሮ በመከናወን ላይ ይገኛል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች የሚኖሩባቸው ትልልቅ የመኖሪያ ሰፈሮች ተገንብተው እየተጠናቀቁ ነው።
ሳዑዲ አረቢያ ይህንን አዲስ ከተማ እንደምትገነባ ይፋ ካደረገች ጀምሮ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እቅዱ የተጋነነ እና ሊተገበር እንደማይችል የሚያስረዱ አስተያየቶች ሲሰሙ ቆይተዋል።
ይህን በተመለከተ ከጥቂት ወራት በፊት አስተያየት የሰጡት የሳዑዲው ልዑል መሀመድ ቢን ሰልማን በሳዑዲ አረቢያ ሊሰሩ የታቀዱ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ አስተያየት የሚሰጡ ብዙ ሰዎች ይህ ሊሳካ የሚችል አይደለም ወይም ከምኞት የማይዘል እቅድ ነው በማለት አስተያየት ይሰጣሉ። እነሱ መናገራቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ እኛ ግን ያሰብነው በማሳካት ስህተታቸውን ማረጋገጣችንን መቀጠል እንችላለን” በማለት በእቅዱ ተግባራዊነት ምንም ጥርጣሬ እንደሌላቸው ገልፀዋል።
ይህ የኒኦም ፕሮጀክት በእቅድ ተይዞ በተለያየ ጊዜ እንደሚጠናቀቅ የተነገረ ሲሆን አጠቃላይ ፕሮጀክቱ እስከ 2045 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በዋሲሁን ተስፋዬ