ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ የገዘፈ ታሪክ፣ ውብ ማንነት፣ ብዝኃ መልክ፣ ባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም እሴት ያለው ህዝብ ሀገር ናት፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያለ ብዝኃ ማንነት ባለበት ሀገር ደግሞ ታይቶ የማይጠገብ በልዩነት ውስጥ የሚንፀባረቅ ልዩ ውበት ጎልቶ ይታያል፡፡
ቱሪዝም ዜጎችን ለማቀራረብ እና ኀብረ-ብሔራዊነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
ቱሪዝም በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ህዝቦችን ለማቀራረብ ጉልህ አበርክቶ አንዲኖረው በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)በኢቢሲ አዲስ ቀን መሰናዶ ላይ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቱሪዝም ታሪክ በተቋም ደረጃ 60 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በዘርፉ ሀገሪቷ መጠቀም የሚገባትን ያህል ሳትጠቀም መቆየቷ አንስተዋል፡፡
ሆኖም ግን ባለፉት ሥድስት ዓመታት ሀገሪቱ ያላትን የቱሪዝም ፀጋዎች የመለየት እና የማልማት ሥራ በማከናወን ውጤት እያስገኘች ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለማሳካት ለምታስበው የወል ትርክት እንዲሁም ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ቱሪዝም የበኩሉን ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል፡፡
መፃዒ የኢትዮጵያ ተስፋ ቁልፍ ቱሪዝም ላይ ነው ያሉት አስጎብኚ እና የቱሪዝም አማካሪ አሸናፊ ካሳ፤ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ዜጎች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ አይነተ ብዙ መዳረሻ ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንደኛዋ መሆኗን በመጥቀስ፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ በይበልጥ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ይህን ግንዛቤ ለማሳደግም በትምህርት ቤቶች ከሀገርን እንወቅ ክበባት ጀምሮ በተለያየ መልኩ ሊሰራበት እንደሚገባ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ልዩነት የመዋብ ምልክት ነው ያሉት አቶ አሸናፊ፤ በልዩነት ውስጥ ያለው አንድነት ከውበት አልፎ ኃይል ይሆናል ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ጋዜጠኛ እና የኢትዮጵያ የባሕል እና ቱሪዝም የጋዜጠኞች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አስናቀ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ባህል፣ እሴት፣ ቋንቋ እንዲሁም የሚያስደምም ሥነ ምህዳር ባለቤት በመሆኗ በልዩነት ውስጥ የምትደምቅ ሀገር ናት ብለዋል፡፡
በብዝኃነት ውስጥ ያለውን ውበት ለመረዳት ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አካባቢዎች ያሏቸውን የተፈጥሮ ሀብት እና ባህል ሊጎበኙ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ