በሞሮኮ ራባት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ኢትዮጵያ ግዙፉን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ለዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ለባለሃብቶች በይፋ አስተዋውቃለች።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ "የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ የአቪዬሽን ጉዞ ታሪካዊ ጅምር ነው" ብለዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በዘላቂ ዲዛይን ሲገነባ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል እንዲሁም አህጉሪቱን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ ዋና በር እንደሚያደርጋትም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የዚህ ፕሮጀክት ዋና የፋይናንስ ሃብት አሰባሳቢ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት በተደረገው የፕሮጀክት ትውውቅ ላይ ከአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ እና እስያ የተውጣጡ አበዳሪዎች እና ባለሀብቶች በፕሮጀክቱ ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው ተመላክቷል።
ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአፍሪካ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ላይ ያለውን እምነት የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ሜጋ ፕሮጀክቱ ከዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ተቋማት፣ ከንግድ ባንኮች፣ ከኤክስፖርት-ክሬዲት ኤጀንሲዎች እና ከኢንቨስትመንት ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት እና ተቀባይነትን አግኝቷል።
በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ተገኝተው ገለጻ አድርገዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም