የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አራት ዓመታትን ሊደፍን ጥቂት ወራት ብቻ ቀርተውታል፡፡
በጦርነቱ በሁለቱም ወገኖች ላይ የደረሰው ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዳለ ሆኖ በዓለም ላይ የፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ዓለም የጦርነቱን መቋጫ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡
ጦርነቱን ለማብቃት የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረጉም አንዳቸውም ግን ሊሳኩ አልቻሉም፡፡ በተለይም ቱርክዬ የሁለቱ ሀገራትን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ብታወያይም ከምርኮኞች ልውውጥ ያለፈ ጠብ ያለ ነገር አልተገኘበትም፡፡
በሰኔ 2024 ከ100 በላይ የሀገራት እና ድርጅቶች ተወካዮች የተሳተፉበት "የዩክሬን የሰላም ጉባኤ" በስዊዘርላንድ ተደርጎ ነበር፡፡ የጉባኤው ዓላማ በተመድ ቻርተር መሰረት የዩክሬን የግዛት አንድነትን በጠበቀ መልኩ የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ ቢሆንም ውጤት ግን አላመጣም።
ዩክሬን በበኩሏ አሥር ነጥቦች ያሉት የሰላም ስምምነት ዕቅድ በ2022 የቡድን 20 ጉባኤ ላይ አቅርባ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ በኩልም የመጣ ለውጥ የለም፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል ከገቡባቸው ጉዳዮች አንዱ የሩሲያ-ዩክሬንን ጦርነት ማብቃት ነበር፡፡
በቃላቸው መሰረት ሁለቱን መሪዎች በማነጋገር እና ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ሀገራቱን ወደ ሰላም ድርድር ለማምጣት ጥረት ቢያደርጉም እስከ አሁን አልተሳካላቸውም፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሁንም ባለ 28 ነጥብ የሰላም ዕቅድ አቅርበው የሁለቱ ሀገራት መሪዎችን ይሁንታ እየጠበቁ ናቸው። በአሜሪካ እና በሩሲያ ባለሥልጣናት እንደተዘጋጀ የሚነገርለት ይህ ባለ 28 ነጥብ የሰላም ዕቅድ በመሪዎች ደረጃ የሚደረግ ድርድርን የሚያካትት ነው።
ለመገናኛ ብዙኃን ሾልኮ ወጣ የተባለው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ዕቅዱ ለሩሲያ ያደላ እንደሆነ የዩክሬን አጋሮች በሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ትችት እየደረሰበት ይገኛል።
ዕቅዱ ዩክሬን እንደ ዶኔትስክ፣ ክሬሚያ እና ሉሃንስክ ያሉ ግዛቶችን ለሩሲያ እንደምትለቅቅ፣ የጦር ኃይሏን ቁጥር እንደምትመጥን እና የሰሜን አትላንትክ ጦር ቃልኪዳን (NATO) የመቀላቀል ሀሳቧን እንድትተው የሚስገድዳት እንደሆነ የምዕራባውያን ሚዲያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ።
የአሜሪካ እና ዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጄኔቫ እና በአቡ ዳቢ ስብሰባዎችን ካደረጉ በኋላ ዕቅዱ ተሻሽሎ ወደ 19 ነጥብ ማዕቀፍ መውረዱን ደግሞ የዘጋርዲያን መረጃ ያመላክታል።
ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት ይህ የተሻሻለው ሰነድ ከዩክሬን ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚስማማ ነው፡፡ በተለይም የግዛት ሉዓላዊነቷን እና የደኅንነት ዋስትናዋን በተመለከተ የበለጠ የተጣጣመ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
የዩክሬን ባለሥልጣናትም በተሻሻለው ዕቅድ መስማማታቸውን እና ስምምነቱ ሙሉ እንዲሆን ግን በዋና ዋና የግዛት ጉዳዮች ላይ በመሪዎች ደረጃ ውሳኔ ማግኘት አለባቸው እያሉ ነው።
ሩሲያ በበኩሏ የመጀመሪያዎቹ የስምምነት ሀሳቦች ለንግግር መንገድ ሊከፍቱ ይችላሉ የሚል ጥንቃቄ የተሞላበት ሀሳብ ሰጥታ የነበረ ሲሆን፣ ዕቅዱ ወደ 19 ነጥቦች ከተስተካከለ በኋላ ግን ስምምነት ላይ ለመድረስ ጊዜ የሚወስድ ነው በማለት ጥርጣሬዋን ገልጻለች፡፡ ይህ ጥርጣሬ የተሞላበት የሩሲያ አቋም ጉዳዩን ውስብስብ እንደሚያደርገው ነው ተንታኞች እየገለጹ ያሉት፡፡
የሆነው ሆኖ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የተቀሩትን ዝርዝር ጉዳዮች ለማጠናቀቅ ከዩክሬን እና ከሩሲያ ልዑካን ጋር የከፍተኛ ደረጃ ስብሰባዎችን ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የመጨረሻዎቹን ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ግን ቅድሚያ በአሜሪካ እና በዩክሬን መሪዎች መካከል ውይይት እንዲደረግ በዩክሬን በኩል ጥያቄ ቀርቧል።
በለሚ ታደሰ