በሩስያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ሩስያም ሆነች ዩክሬን የደረሰባቸው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ቀላል አይደለም።
በእርግጥ በጦርነቱ ምክንያት ሚሊዮኖች ለከፍተኛ የምግብ ዕርዳታ መዳረጋቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) መረጃ ያመለክታል።
ሁለቱም ወገኖች ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ስኬቶች እንዳገኙ እየገለፁ ቢሆንም በራሳቸውም ሆነ በዓለም ላይ ያመጣው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በጦርነቱ ምክንያት የዋጋ ግሽበት፣ አስከፊ ድህነት፣ የምግብ ዋስትና እጦት እና የአካባቢ መራቆት እየተባባሰ መጥቷል ብሏል።
እንደ የዓለም ባንክ መረጃ ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሚሊዮን ወደ 700 ሚሊዮን ገደማ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች እጅግ የከፋ ነው።
በአውሮፓ ደረጃ ተመጣጣኝ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዋጋ ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ 80 በመቶ መጨመሩም ነው የሚጠቀሰው።

በጦርነቱ የተነሳ የዓለም ዕድገት ደረጃ በ1 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ የዋጋ ግሽበቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2 በመቶ ከፍ ማለቱን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።
ሁለቱ ሀገራት በጋራ 30 በመቶ ገደማ የስንዴ ምርት ለዓለም የሚያቀርቡ በመሆናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የምግብ እህል አቅርቦት ዋጋ በ12.6 በመቶ አሻቅቧል።
እናም በተለያዩ ወገኖች ሲደረጉ የነበሩ የሰላም ጥረቶች ከሁለቱ ወገኖች ጀርባ ባሉ አካላት ምክንያት ሲደናቀፉ ቢቆይም ጦርነቱ እንዲያበቃ ግን የሁሉም ወገኖች ፍላጎት ነው።
አሁን በአሜሪካ ሁለቱ ሀገራት ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናትም የሰላም ዕቀዱን የመቀበል አዝማሚያ እያሳዩ ነው። ይህ ደግሞ ዓለምን ከብዙ ስጋቶች እንደሚታደግ ነው እየተጠቀሰ ያለው።
ጦርነቱ ማብቃቱ ለዓለም ኢኮኖሚ፣ ደኅንነት እና ሰብዓዊ ሁኔታ ትልቅ ትርጉም አለው። ለኢኮኖሚ መረጋጋት፣ ዓለም አቀፍ ደኅንነት እና የሰብዓዊ እርዳታ መሻሻልም አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የፖለቲካ ተንታኞች የሚጠቅሱት።
ዩክሬን እና ሩስያ የግብርና ምርቶች በተለይም የስንዴ፣ የበቆሎ እና የሱፍ ዘይት ዋና ዋና አቅራቢዎች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ሩስያ እንደ አፈር ማዳበሪያ ያሉ የግብርና ግብዓቶች አቅራቢ የነበረች በመሆኗ፤ በጦርነቱ ምክንያት የናረው የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ጦርነቱ ቢቆም እንደሚሻሻል ይጠበቃል።
ጦርነቱ ማብቃቱ በጥቁር ባሕር በኩል እህል መላክ የሚያስችል በመሆኑ አቅርቦትን በመጨመር የሸቀጦች ዋጋን ከማረጋጋቱ በተጨማሪ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ወገኖች እፎይታ ይሰጣል።
ሩስያ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ እና ነዳጅ አቅራቢ ብትሆንም በጦርነቱ ምክንያት በተጣለባት ማዕቀብ የተነሳ ምርቱን መላክ ባለመቻሏ ከፍተኛ እጥረት ተከስቷል። የጦርነቱ ማብቃት ለዚህ ችግርም መፍትሔ የሚሰጥ ይሆናል።
ግጭቱን ማስቆም የሩስያ ጋዝ በአውሮፓ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢነርጂ ገበያን ለማረጋጋት ስለሚረዳ የማሞቂያ፣ የኃይል ማመንጫ እና የመጓጓዣ ወጪን በዓለም ዙሪያ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ጦርነቱ እና ተያያዥ ማዕቀብ በፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎች እና ማሽነሪዎች ዝውውር የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳርፏል። ሰላም እነዚህን ገደቦች በማቃለል የማኑፋክቸሪንግ እና የምርት ቅልጥፍናን ያሳድጋል።
የምዕራባውያን መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለዩክሬን ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር አውጥተዋል። ግጭቱን ማስቆም የሀገራቱ የአደጋ ጊዜ ወጪ እንዲቀንስ በማድረግ ገንዘቡ ለልማት እንዲውል ያስችላል።
ጦርነቱ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የነበረውን የፀጥታ ሥርዓት መሰረት ያናወጠ ሲሆን፣ ፍጻሜው ዓለም አቀፍ ሕግን ማክበር እና መረጋጋትን ሊያመጣ እንደሚችል ነው የሚጠቀሰው።
ጦርነቱን ተከትሎ የመጣው ሌላው ችግር ከፍተኛ የኑክሌር አደጋዎች ስጋት መጨመር ነው። ሩስያ በዓለም ቀዳሚዋ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ታጣቂ መሆኗ ደግሞ ግጭቱ ተባብሶ የሕልውና አደጋ ተደቅኖብኛል ካለች እንደ ቆሰለ አውሬ የምትወስደው እርምጃ አስፈሪ ሊሆን ይችላል የሚለው ሐሳብ ነው የፍርሃቱ ምንጭ። ግጭቱ ግልጽ እና ስውር የኑክሌር ፉክክሮችን ያካተተ ሲሆን፣ በሩስያ እና በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት መካከል ቀጥተኛ ግጭት የመፍጠር ስጋትን ከፍ አድርጎት ነበር።
የጦርነቱ መቆም በቀጣናው በሚገኙ እንደ ዛፖሪዝሂያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በመሳሰሉት ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ዙሪያ ያሉ አደጋዎችንም ይቀንሳል።
በጦርነቱ ምክንያት ዩክሬን ውስጥ እየፈሰሰ ያለው ሀብት በማዳን የዲፕሎማሲ፣ ወታደራዊ እና የፋይናንስ ብክነቶችን ያስቀራል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዩክሬን ስደተኞች ኑሮአቸውን እንደገና ለመጀመር ወደ አገራቸው የመመለስ ዕድል ያገኛሉ።
በለሚ ታደሰ