በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት የብሪክስ አገራት የቱሪዝም ገበያ በእጥፍ ሊያድግ ይችላል። የእንግዳ ተቀባይነት ዘርፉ ሊያጋጥሙት የሚችሉ ፈተናዎች ምንድን ናቸው? ዕድገቱንስ ሊያደናቅፉ የሚችሉ ነገሮች ምን ይሆኑ?
በአውሮፓውያኑ 2025 የውጭ ቱሪስቶች ለብራዚል ሪከርድ ነው የተባለ ገቢ አስገኝቷል። ኢንዶኔዢያ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የቱሪስቶች መምጣት በ10 በመቶ መጨመሩን ሪፖርት አድርጋለች። ቻይና ቪዛ መሰረዟን ተከትሎ የሩሲያ ቱሪስቶች መዳረሻ እየሆነች ነው። ሩሲያ ደግሞ የንግድ ጉዞን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች። የብሪክስ አገራት ተወዳጅ የጉዞ መዳረሻዎች እየሆኑ ያሉት ለምንድን ነው? ይህ በእነዚህ ሀገራት ኢኮኖሚ፣ ሥነ-ምህዳር እና ማኅበራዊ ልማት ላይስ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል? ጥቂት እንመልከት፦

ብራዚል
በአማዞን ተፋሰስ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች፣ ውብ ሸለቆዎች እና የሳንታ ካታሪና ተራሮች፣ በዓለማችን ትልቁ የኢጓዙ ፏፏቴ፣ እና በእርግጥም ሪዮ ዴጄኔሮ ደማቅ የከተማ ዳርቻዎቿ እና ታዋቂ ካርኒቫል ያላት ብራዚል ለቱሪስቶች እጅግ በጣም ከሚፈለጉ አገራት አንዷ እየሆነች ነው።
ከጥር እስከ መስከረም 2025 ባሉት ዘጠኝ ወራት የውጭ ተጓዦች ለሀገሪቱ 6 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ አስገኝተዋል። ይህም እስከ አሁን ከተመዘገበው ሁሉ ከፍተኛው አሃዝ ሲሆን፣ ከ2024 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ11.7 በመቶ ብልጫ እንዳለው የብራዚል ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ ገቢ የተገኘው ቱሪስቶች ለሀገር ውስጥ ጉዞ፣ ለመጠለያ፣ ለምግብ፣ ለመዝናኛ እና ለግዢ ወጪ በማድረጋቸው ነው። አብዛኞቹ ተጓዦች የውጭ አገር ዜጎች ሲሆኑ፣ ብራዚል ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን በመሳብ ታሪካዊ ሪከርድ ማስመዝገቧን ተረጋግጧል። 7 ሚሊዮን በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች በዓመቱ የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ጎብኝተዋል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ45 በመቶ የበለጠ ነው።
በሚንዙ የቻይና ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርክ ሃዋርድ ሌቪን ለቲቪ ብሪክስ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ የብራዚል በቻይና ቱሪስቶች ዘንድ ተወዳጅነት ማደጉን ጠቁመዋል።
ማርክ ሌቪን "በብራዚል የቱሪዝም እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን እናያለን። የቻይና ቱሪስቶችን ቁጥር ስንመለከት፣ ከ2023 እስከ 2024 በ80 በመቶ ጨምሯል" ብለዋል።

ኢንዶኔዢያ
ኢንዶኔዢያም የቱሪዝም ሪከርዶችን ሪፖርት አድርጋለች። በ2025 የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ሀገሪቱ 11.4 ሚሊዮን ቱሪስቶችን ተቀብላለች። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ10.2 በመቶ ብልጫ አለው ሲል የቲቪ ብሪክስ አጋር የሆነው ዢንዋ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በመስከረም ወር ብቻ 1.4 ሚሊዮን የውጭ አገር ዜጎች ኢንዶኔዢያን ጎብኝተዋል። ሀገሪቱ በሩሲያውያን ዘንድም በፍጥነት ተወዳጅነት እያገኘች ነው። ከጥር እስከ ሰኔ 2025 ባሉት ወራት 117 ሺህ በላይ የሩሲያ ቱሪስቶች ጎብኝተዋል፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት በ35.4 በመቶ ብልጫ ያለው ሆኖ ተመዝግቧል።

ቻይና
ቻይና በአውሮፓውያኑ 2025 መኸር ለሩሲያ ቱሪስቶች በጣም ተወዳጅ መዳረሻ መሆን ችላለች።
ለሩሲያውያን የሙከራ የነጻ ቪዛ አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ ተወዳጅነቷ የታይላንድን ተወዳጅነት ተጠግቷል።
ከሩሲያ ተጓዦች ለቻይና ጉዞዎች የነበረው ፍላጎት በ50 በመቶ ጨምሯል። ባህላዊ የጉዞ መስመሮች (ቤጂንግ እና ሻንጋይ) እንዲሁም የምግብ ቱሪዝም፣ የስነ-ምህዳር ቱሪዝም፣ እና ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች እና የንግድ ዝግጅቶች ጉዞዎች ተወዳጅ ነበሩ።
ማርክ ሃዋርድ ሌቪን "የቪዛ-ነጻ መዳረሻን ለረጅም ጊዜ ማስፋፋት ለቱሪስቶች እንደ ግብዣ ነው። ቻይና ሰፊ ልዩ ልዩ አማራጮችን ትሰጣለች፤ ከባህላዊ ፕሮግራሞች በተለይም ብሔረሰቦች በሚገኙባቸው አካባቢዎች እስከ ክረምት ቱሪዝም እና 'ቀይ' ቱሪዝም ድረስ ብዙ አማራጮችን አቅርባለች። አዲስና ዘመናዊ አየር ማረፊያዎች እና የከፍተኛ ፍጥነት ባቡር ኔትወርክ ልማትም የቻይናን ቱሪዝም እድገት ይደግፋል" ብለዋል።

ሩሲያ
በሩሲያ የእንግዳ ተቀባይነት ዘርፍ ዋና ትኩረት የንግድ ቱሪዝም እየሆነ ነው። የውጭ አገር ዜጎች በአብዛኛው የሚጓዙት ከብሪክስ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዙ መድረኮች እና ኮንፈረንሶች ላይ ለመሳተፍ ነው።
በሙርማንስክ፣ ሳክሃሊን፣ ሴንት ፒተርስበርግ እና ሞስኮ እንደዚህ አይነት ዝግጅቶች እና መድረኮች እየሰፉ ነው። የፕሮግራሙ አዘጋጆችም ብዙውን ጊዜ የባህል እና የምግብ ቱሪዝምን ያካትታሉ፤ የክልል ባለሥልጣናት ደግሞ ጎብኚዎች ከጓደኞቻቸው እና ከቤተሰባቸው ጋር በግል እንዲመለሱ ለማድረግ ያለሙ ናቸው።
የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት የንግድ መዋቅሮች እና ሥራ ፈጣሪዎች ጥምረት ፕሬዝዳንት የሆኑት ሉባርቶ ሳርቶዮ "የንግድ ቱሪዝም፣ በእኔ እይታ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የቱሪስት ፍሰት ይይዛል፤ ይህ ከቱሪዝም ውጪ በብዙ ዘርፎች የብሪክስ አጋርነት መስፋፋት ውጤት ነው" ብለዋል።
የሩሲያ ሆቴል ባለቤቶችም ባለፉት ሁለት ዓመታት የእንግዳ ስብጥር ለውጥ መኖሩን ይገልጻሉ። ዋናዎቹ ቱሪስቶች አሁን የሚመጡት ከዩኤኢ፣ ቻይና፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኢራን እና ህንድ ሲሆን ይህም በቪዛ ፖሊሲ ለውጦች እና በኤሌክትሮኒክ ቪዛዎች እድገት የተደገፈ ነው።

ህንድ
ህንድም ልክ እንደ ብዙዎቹ የብሪክስ አገራት የቱሪስቶች ቁጥር መጨመር እያየች ነው። በአውሮፓውያኑ 2024 ሪከርድ የሆኑ 9.9 ሚሊዮን የውጭ ቱሪስቶች ጎብኝተዋል ሲል የህንድ ቱሪዝም ሚኒስቴር ዘግቧል።
መንግሥት ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኤግዚቢሽኖች ላይ ከጉብኝት አዘጋጆች ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ ዘመቻዎችን ማስኬድ እና ቀጥታ በረራዎች አማካኝነት የአየር ትስስርን ማሻሻል ላይ ያተኩራል።
ማርክ ሃዋርድ ሌቪን "በህንድ ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ከ2014 እስከ 2024 በአሥር ዓመታት ውስጥ በእጥፍ አድጓል፤ ይህ የሆነው በብዛት ባሉት ታሪካዊ ቦታዎች እና ለ170 ለሚሆኑ አገራት ዜጎች በ72 ሰዓታት ውስጥ የሚሰጡ የኤሌክትሮኒክ ቪዛዎች በመስፋፋት ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ
ባለፉት አምስት ዓመታት የተመድ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር በ40 በመቶ ጨምሯል።
መንግሥት ቱሪዝምን ለኢኮኖሚ ልማት ቅድሚያ ሰጥቷል፣ ዓለም አቀፍ መንገዶችን እና በረራዎችን አሻሽሏል፣ አዲስ አበባን ወደ መተላለፊያ ማዕከልነትም ቀይሯል።
ኢትዮጵያ በምግብ እና በቡናዋም የምትታወቅ መሆኗ ከቱሪዝም አቅርቦቶች ጋር ተዳምሮ የኦብኚዎችን ቀልብ ይዛለች።

ደቡብ አፍሪካ
በአውሮፓውያኑ 2024 ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር በ5.1 በመቶ ጨምሮ 8.92 ሚሊዮን ደርሷል ሲል የቲቪ ብሪክስ አጋር የሆነው ዢንዋ የዜና ወኪል የሀገሪቱን ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።
ደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ልምዶችን ትሰጣለች፣ ከእነዚህም መካከል የሳፋሪ ጉዞዎች፣ የሻርክ ዳይቪንግ፣ የባህር ዳርቻ ዕረፍት እና የወይን ቱሪዝም ይገኙበታል።

ሌሎች የብሪክስ አገራት
ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ማደጉን የቀጠለ ሲሆን፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት ከነበረው ደረጃ አልፏል። በአውሮፓውያኑ 2025 የመጀመሪያ አጋማሽ ወደ 690 ሚሊዮን የሚጠጉ ቱሪስቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጉዘዋል። ይህም ከአንድ ዓመት በፊት በ5 በመቶ ብልጫ እንዳለው የተመድ ቱሪዝም ሪፖርት አድርጓል።
ብዙ የብሪክስ አገራት በቱሪዝም ላይ ኢንቨስት እያደረጉ ነው። ኢራን በአውሮፓውያኑ 2024 ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድባለች። አብዛኛው ለመጠለያ ማስፋፊያ፣ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎችን ጨምሮ ለመገንባት ነው።

ግብፅ በ2030 በየዓመቱ 30 ሚሊዮን ቱሪስቶችን ለማስተናገድ አቅዳለች። በ2025 የመጀመሪያ አጋማሽ 5 ሺህ አዲስ የመኝታ ክፍሎች ታክለው በዓመቱ መጨረሻ ተጨማሪ 18,000 ለማድረስ ታቅዷል፤
ዱባይ በ2030 የሚመጡ ጎብኚዎችን ቁጥር ወደ 40 ሚሊዮን ለማሳደግ አቅዳለች፣ ይህም ለኢኮኖሚው በግምት 108 ቢሊዮን ዶላር አስተዋጽኦ ያደርጋል።
የዘላቂ ቱሪዝም ጥቅሞች
ቱሪዝም ከኢኮኖሚ ባለፈ ለብሪክስ ትርፋማ ነው፣ ብዙውን ጊዜ የቴክኖሎጂ እድገትን እና የስነ-ምህዳር መሻሻልን ያመጣል።
ማርክ ሃዋርድ ሌቪን "ዘላቂ ቱሪዝም አካባቢን ለመጠበቅ እና ሀብቶችን በብቃት ለመጠቀም ይረዳል። አንዳንድ ሆቴሎች የፀሐይ ወይም የንፋስ ኃይልን ይጠቀማሉ እንዲሁም የህዝብ ትራንስፖርትን ያበረታታሉ" ብለዋል።
ዘላቂ ቱሪዝም ዲጂታል ቴክኖሎጂን፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና ቢግ ዳታን የሚያቀናጁ ስማርት ከተሞችን ይደግፋል። ዝቅተኛ ካርበን ልቀት ያለው ትራንስፖርት ቁልፍ ነው።
ቻይና በኤሌክትሪክ ትራንስፖርት እየመራች ሲሆን 22 ሚሊዮን የኤሌክትሪክ መኪኖች 6 ሺህ ኤሌክትሪክ አውቶቡሶች እና 3.9 ሚሊዮን ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች (1.2 ሚሊዮን ፈጣን ቻርጀሮችን ጨምሮ) አሏት።

ህንድ፣ ሩሲያ እና ብራዚል ከዚህ ያነሰ የኤሌክትሪክ መኪኖች ያሏቸው ቢሆንም ከቻይና ውጪ ህንድ ከፍተኛው የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ቁጥር (8,400)፣ ደቡብ አፍሪካ (2,200) እና ሩሲያ (1,882) በመያዝ ይከተላሉ።
ሌሎች የብሪክስ አገራትም የኤሌክትሪክ ትራንስፖርትን በማልማት ላይ ናቸው።
ቱሪዝም እና ባህል
የብሪክስ ቱሪዝም የባህል ልውውጥን ያበረታታል። የቪዛ ቅልጥፍና፣ ዲጂታል አገልግሎቶች እና የመረጃ ልውውጥ መጨመር ርቀቶችን፣ የገቢ ደረጃዎችን እና የባህል ልዩነቶችን ሳይገድብ ሕዝቦችን እንደሚያቀራርብ ይታመናል።
ፈተናዎች እና አደጋዎች
በቱሪዝም መስክ ትላልቅ የጋራ የብሪክስ ፕሮጀክቶች የቅርብ ጊዜ ጉዳይ ናቸው። ሆኖም፣ የአባል አገራት የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እጅግ ተስፋ ከሚሰጡት ውስጥ አንዱ መሆኑ ግልጽ ነው።

ለቱሪዝሙ እድገት ምክንያቶች ደግሞ የብሪክስ አገራት ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሆኑ አንዱ ነው። ከእነዚህም መካከል አማካይ የገቢ ደረጃ ያላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣትና ንቁ ሰዎች ይገኙበታል። ከዚህም በላይ በብሪክስ አገራት የተማረው ሕዝብ ድርሻ እየጨመረ ሲሆን ይህ ደግሞ ለባህላዊ እና ትምህርታዊ ቱሪዝም ልማት አንቀሳቃሽ ኃይል ነው።
በተመሳሳይ ጊዜ፣ የቱሪዝም ዘርፉን በማስፋፋት ጎዳና ላይ፣ የብሪክስ አገራት ለበርካታ ፈተናዎች ሊጋለጡ ይችላሉ።
ከመንገድ፣ ከሆቴሎች እና ከአየር ማረፊያዎች ልማት ጋር የተያያዙ መሠረተ ልማታዊ ችግሮች አሉ። ሁሉም አገራት ለዚህ የሚያስፈልገው ሀብት የላቸውም።

እንዲሁም ወደ ትርፋማ ሊሆን የሚችል የቱሪዝም ገበያ የሚገቡ አገራት በጨመሩ ቁጥር፣ በመካከላቸው ያለው ውድድር እየጨመረ ይሄዳል፣ ቱሪስቶችም የበለጠ መርጠው የሚጓዙ ይሆናሉ።
ይህ ማለት የብሪክስ አገራት የቱሪዝም ዘርፍ፣ ሊኖረው የሚችለው ትርፋማነት እና ተስፋ ቢኖርም የተቀናጀ አቀራረብ፣ የጋራ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት፣ ሠራተኞችን ማሠልጠን፣ እና ቴክኖሎጂዎችንና የከተማ መሠረተ ልማትን ማዘመን ይፈልጋል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል።
በሰለሞን ገዳ