የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ እና ዩክሬንን የሰላም ስምምነት ዙሪያ በአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከተመራ ልዑክ ጋር ዛሬ ይወያያሉ።
በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበው ባለ 28 ነጥብ የሰላም ስምምነት ዙሪያ የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለስልጣናት ለሁለት ቀናት በፍሎሪዳ ከተወያዩ በኋላ አሁን ደግሞ ከሩሲያ ጋር ለመወያየት የአሜሪካ ልዑክ ወደ ሞስኮ አቅንቷል።
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ ያቀረበችውን ረቂቅ የሰላም እቅድ በዝርዝር ማየታቸውን እና ጦርነቱን ለማስቆም የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዝርዝር ጉዳዮችን ደግሞ በዛሬው ውይይታቸው እንደሚመለከቷቸው ፕሬዝዳንቱ መግለፃቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በፍሎሪዳ የተካሄደውን ውይይት ገንቢ በማለት የገለጹት ሲሆን፤ አሁንም መታየት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አንስተዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ካጃ ክላስ እና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቱን ወደ ሰላም ስምምነት ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት ያደነቁ ሲሆን አራት አመት ሊያስቆጥር ጥቂት ጊዜ የቀረው ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጫ እንዲያገኝ ጠይቀዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#ebcdotstream #Russia #America #Ukraine #Peaceagreement