የግብርና ኬሚካል ርጭትን በአውሮፕላን እና በድሮን ታግዞ ማከናወን ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ውጤታማ እንደሚያደርግ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።
በአንጻሩ በጀርባ ላይ ታዝሎ የሚደረግ የማሣ ላይ ኬሚካል ርጭት በርካታ ተያያዥ ጉዳቶችን ያስከትላል። በተለይ ኬሚካሉን በሚሸከሙ ሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከዚህ ባለፈ የአየር ላይ ኬሚካል ርጭት በውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ የሚመጣውን ኬሚካል በአግባቡ ለመጠቀም ወሳኝ ስለመሆኑ ይነገራል።
በዚህ ረገድ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ፀረ አረም እና ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን በዘመናዊ የአየር ላይ ርጭት ማከናወን ጉልህ ሚና እንዳለው የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የዕፅዋት ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ ደጀኔ ሄርጳ ገልፀዋል።
የተለያዩ የአረም ዝርያዎች በሰብሎች ላይ በተለይ በስንዴ እና ገብስ ላይ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን በአውሮፕላን በታገዘ የፀረ አረም እና ፀረ ተባይ ርጭት መቆጣጠር እንደሚቻል ተናግረዋል።
እነዚህ ዘመናዊ እና ፈጣን አውሮፕላኖች በአጭር ጊዜ ሰፊ ሄክታር ማሳን የመሸፈን አቅም አላቸው ሲሉ የናሽናል ኤርዌይስ ሥራ አስኪያጅ ገዛኸኝ ብሩ ገልፀዋል።
ሥራው የሚያከናውኑ አምስት አውሮፕላኖች አሉን ያሉት ሃላፊው፤ አንድ አውሮፕላን በአማካኝ የአየር ፀባዩ ተፅዕኖ ካልፈጠረበት 1200 ሄክታር ማሳ ላይ ኬሚካል መርጨት እንደሚችል አስረድተዋል።
በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ድርጅት ውስጥ እና በተለያዩ አካባቢዎች በዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመጠቀም የኬሚካል ርጭት መደረጉ ምርትን በማሳደግ ውጤት እያሳየ መሆኑ ተመላክቷል።
በሄለን ተስፋዬ