Search

ኢትዮጵያ ለግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቦች ምንም ቦታ የላትም - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ረቡዕ ኅዳር 24, 2018 322

ግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቦች ላይ ተንተርሳ በዓባይ ወንዝ ላይ ለምትከተለው የተሳሳተ እሳቤ ኢትዮጵያ ምንም ቦታ እንደሌላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ በቅኝ ግዛት ዘመን እሳቤ ውስጥ ያሉ የግብፅ ባለስልጣናት በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን የተሳሳተ አቋም አሁንም እያንጸባረቁ ነው ብሏል፡፡

የሀገሪቱ ባለስልጣናት የሁለትዮሽ ድርድሮችን ወደ ጎን በመተው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጩት መሰረት ቢስ ውንጀላ ተቀባይነት እንደሌለውም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የግብጽ መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው ባሉ ሀገራት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት በማድረግ ላይ ይገኛል ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ይህን የተሳሳተ እና ጊዜው ያለፈበት አካሄድ እንደማትቀበለው አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒዝምን እና በአህጉሪቱ ውስጥ የጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎችን በመደገፍ ረጅም እና አኩሪ ታሪክ ያላት ሀገር ናት ያለው መግለጫው፤ ግብጽ እንደ ሀገር በዓባይ ወንዝ ላይ ለምትከተለው የተሳሳተ እሳቤ ኢትዮጵያ ቦታ የላትም ብሏል።

የዓባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች የሚመነጭ እና 86 በመቶ የሚሆነው የናይል ተፋሰስ ውኃ ከኢትዮጵያ እንደሚሄድ የሚታወቅ መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው፤ ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ይህን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት አላት ብሏል።

ዓለም አቀፍ ህጎችን አክብራ እየሰራች የምትገኘው ኢትዮጵያ በድንበሯ ውስጥ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም ከማንም ሰው ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ እንደሌለባት ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

ግብጽ ውይይቶችን እና ድርድሮችን በተደጋጋሚ ውድቅ ስታደርግ መቆየቷን የገለፀው ሚኒስቴሩ፤ አሁን ላይ ሀገሪቱ ከዚህም አልፋ ግጭቶችን በማቀነባበር የጥላቻ ንግግሮችን በማሰማት ስራ ላይ ተጠምዳለች ብሏል፡፡

ይህ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር በሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ሊወገዝ እንደሚገባውም ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ በራስ የመተማመን እና የእድገት ምሳሌዎች ናቸው ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በልማት እና በትብብር ማዕቀፍ ከሁሉም ሀገራት ጋር ለመስራት ዝግጁ እንደሆነች አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ አሁን ያለውም ትውልድ ሆነ የሚመጣውን ትውልድ ፍላጎቶች ለሟሟላት በፍትሀዊነት ላይ የተመሰረተ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሔዎች ላይ መስራቷን ለማረጋገጥ በጽኑ ትቆማለች ሲልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አመልክቷል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ