የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የገቢ ምንጭን በማሳደግ፣ የተራቆቱ መሬቶችን በመመለስ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከሚተከሉ ችግኞች መካከል የደን፣ የፍራፍሬ፣ የመኖ እና ሌሎችም ችግኞች እንደሚገኙበት ጠቅሰው፣ በተለይ በዚህ ዓመት ለየት ባለ መልኩ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች በተደራጀ መንገድ በክላስተር እንዲተከሉ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
"ተስፋን እንተከል" በሚል መሪ ሐሳብ በሚከናወነው የዘንድሮው አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር፣ ማኅበረሰቡ ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጄ ማንደፍሮ በበኩላቸው፣ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች ከ10 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን በማስታወስ፣ በዚህም የክልሉ የደን ሽፋን ከነበረበት 14.6 ወደ 18.9 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
በተከላ መርሐ ግብሩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የአካባቢው አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
በሳሙኤል ወርቅአየሁ