የኤርትራ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት ኢትዮጵያን በማዳከም እና በማፍረስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
አቶ ጌታቸው ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ያዘጋጀው ዓመታዊ የብሔራዊ ደኅንነት ኮንፍረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ይህ በምሥጢር የሚያዝ ሳይሆን በአደባባይ የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኤርትራን ወደ ነጻነት እንቅስቃሴ ያስገቡት ኃይሎች ኢትዮጵያን ማዳከም የፈለጉ ኃይሎች መሆናቸውን አስታውሰዋል።
የኤርትራ የሀገርነት ሕልውና መረጋገጥ ሁሌም ኢትዮጵያን ከማዳከም ስሌት ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን አንሥተዋል።
የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አፍራሽ ኃይሎችን በማደራጀት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት መረጋጋት እንዳይኖር በመሥራት ኢትዮጵያ ላይ የደኅንነት ስጋት ሲደቅን መቆየቱ በተግባር መታየቱን ገልጸዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ያሉ ጉድለቶች ላይ አተኩረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በወንድወሰን አፈወርቅ