Search

ከሕንድ ጋር ያለንን የንግድ ልውውጥ 100 ቢሊየን ዶላር ማድረስ እንፈልጋለን - ፑቲን

ዓርብ ኅዳር 26, 2018 93

ሩሲያ ከሕንድ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ በፈረንጆቹ እስከ 2030 ድረስ 100 ቢሊየን ዶላር የማድረስ ፍላጎት እንዳላት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለፁ።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሕንድ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ከአራት ዓመታት በኋላ ኒው ዴልሂ ገብተዋል።

ፑቲን በሕንድ ጉብኝታቸው ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ሩሲያ ከሕንድ ጋር በኢነርጂ እና በመከላከያ ብቻ ሳይሆን በብዙ ዘርፎች መጠነ-ሰፊ ግንኙነቶችን ማድረግ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡

ሕንድ ከሩሲያ የነዳጅ ዘይት እንዳትገዛ በአሜሪካ እየደረሰባትን ጫና ተከትሎ ሩሲያ ያልተቋረጠ የነዳጅ ጭነት ወደ ሕንድ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገልጸዋል። 

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው፤ በሩሲያ እና ሕንድ መካከል ያለው ግንኙነት በጋራ መከባበር እና መተማመን ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል፡፡

ሀገራቸው በዩክሬን ያለውን ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ማናቸውንም ጥረቶች እንደምታበረታታ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ወደላቀ ደረጃ ለመውሰድ የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጉብኝት ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ሩሲያ እና ህንድ ከነዳጅ አቅርቦት ስምምነት ጎን ለጎን በመከላከያ፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና በሌሎችም ዘርፎች የትብብር ስምምነቶችን መፈራረማቸውን ስፑቲንክ ዘግቧል።

በቢታንያ ሲሳይ

#Ebc #Ebcdotstream #India #Russia