ኢትዮ ቴሌኮም ከካምቴል (CAMTEL) ጋር የካሜሩንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን የሚያስችል ታሪካዊ የማስተር ሰርቪስ የኮንትራት ስምምነት በካሜሩን ያውንዴ ከተማ ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እና የካምቴል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጁዲት ያህ ሰንዴይ የተቋማቱ እና ጥሪ የተደረገላቸው የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት ነው።
ስምምነቱ፣ የካምቴል የሥራ ሃላፊዎች ወደ ሀገራችን በመምጣት ኢትዮ ቴሌኮም በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ" ግንባታ ውስጥ ያሳየውን የላቀ የቴክኖሎጂ አመራር ከተመለከቱ በኋላ፣ ተሞክሮውን ወደ ካሜሩን ለመውሰድ ከነበራቸው ፍላጎት የመነጨ ነው።

በስምምነቱ መሠረት፣ ሁለቱ ኦፕሬተሮች በካሜሩን የፋይናንስ ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ለማስፋፋት፣ ብሔራዊ ክላውድ በመገንባት የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ፣ የሞባይል ኔትወርክ ጥራትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የካምቴልን አሠራር በይበልጥ በማዘመን ደንበኛ ተኮር ባህል ለመገንባት በጋራ ይሠራሉ።
በተጨማሪም ስምምነቱ ለካሜሩን የዲጂታል ኢኮኖሚ ቁልፍ የሆኑ ተቋማት እና ቢዝነሶችን የሚያቀላጥፉ ዲጂታል መፍትሄዎችን፣ የተጨማሪ እሴት እና የኢንተርኮኔክት አገልግሎቶችን በጋራ ለመተግበር ያስችላል።
ስምምነቱ ኢትዮ ቴሌኮም የ“ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028 ስትራቴጂ” መሠረት ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት በማቅረብ እና አህጉራዊ ትብብርን በማጎልበት የዲጂታል አፍሪካ ጉዞን ለማፋጠን የሚያስችል ታሪካዊ ምዕራፍ ስለመሆኑ ተገልጿል።
#Ethiotelecom #Camtel #DigitalAfrica #DigitalCameroon