Search

ምርጫ የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚገለጽበትና ሕዝብ በድምፁ መንግሥት የሚመሠርትበትም ሂደት ነው፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ቅዳሜ ሚያዝያ 24, 2018 51

ምርጫ ለአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ነው፤ የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚገለጽበትና ሕዝብ በድምፁ መንግሥት የሚመሠርትበትም ሂደት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-
ዛሬ በከተማችን አዲስ አበባ 7ኛው አገራዊና ከተማ አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲን ዓላማና ግብ የሚደግፍ፣ የፓርቲውን የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያጎላ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።
ምርጫ ለአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ነው።
የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚገለጽበትና ሕዝብ በድምፁ መንግሥት የሚመሠርትበትም ሂደት ነው።
ያለ ምርጫ መንግስት መመስረት አይቻልም።ያለ ህዝብ ተሳትፎና ውሣኔም አይሰካም።
ብልፅግናም ሊቀጥል የሚችለው በህዝብ ውሣኔ ብቻ ነው።ህዝብ የመወስን ሥልጣኑ ከተረጋገጠለት እና ህዝባችንም ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ ከወሰነ የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያቆመው አይኖርም።
ዛሬ ኢትዮጲያ ውስጥ የመገለል፥ የመጨፍለቅ ወይም በነላይነት የሚነግስበት እድል የለም ። የሁላችንም የሆነች ሃገር እየገነባን ነው ።
በከተማችን አዲስ አበባ ማንንም ያልዘነጋ አካታች የሆነ ልማት እየሠራን እንገኛለን ።አዛውንቶች እፎይ እንዲሉ ፥ ህጻናት ቦርቀው እንዲያድጉ ፥ወጣቶች ተገቢውን ሥራ አግኝተው በአካል እና በአእምሮ ጎልብተው እንዲያድጉ ህልማቸውን እንዲኖሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ገንብተናል።
የከተማችንን ጎስቋላ ገጽታ ለመቀየር በሰራነው ስራ 74 በመቶ የነበረው የጭቃ ቤት ወደ 30 በመቶ አድርሰናል።
ጨለማ የነበሩ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ዛሬ በርተዋል፣ ጠባብ ጎዳናዎች ሰፍተዋል። ለህዝባችን ምቾትን የሚጨምሩና ክብርን የሚጠብቁ እንዲሁም ጤናው እንዲጠበቅ የሚያስችሉ ንጹህ፣ አረንጓዴ ውብ ከተማ በስፋት ገንብተናል። ከአፍሪካ አስር ንጹህ ከተሞች አዲስ አበባ አንዷ እንድትሆንም አድርገናል።
እኛ በምርጫ ወቅት ብቻ ህዝብ ትዝ አይለንም። ህዝብ ውስጥ ነበርን ከህዝብ ጋር ነን ።መንግስት ከመሆናችን በፊት ለህዝብ ታግለናል፣ ህዝባችን እድናገለግለዉ እድል ከሰጠን በኋላም ችግሩን እየተረዳንና በርካታ መፍትሔ ሰጥተናል።
በ7ኛው ዙርም ለሕዝባችን ቃል የምንገባው፣ ከተመረጥን ዘላቂ ሰላምንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ሌት ተቀን በመሥራት ያለምንም መሸራረፍ እንደምንፈጽም ነው።
የብልፅግና ፓርቲ ማኒፌስቶ ትናንትን መልካም አሻራዎች ማስቀጠያ ፣ የከረሙ ችግች ማከሚያ፣ ዛሬን በአግባቡ መጠቀሚያ፣ ነገን መተለሚያና ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት አገር ማሻገሪያ ቃል ኪዳን ነው።
ብልፅግናን መምረጥ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ወጥቶ አስተማማኝ መጻኢ እድልን ለመገንባት መወሰን፤ ብልፅግናን መምረጥ እውነተኛ ዴሞክራሲን መምረጥ ነው።
የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታችን የሆነው የስንዴ ነዶም የመደመር፣ የአንድነት፣ የተባብሮ መሥራት፣ የምርታማነት፣ የተምሳሌትነት፣ የልዕልና እና የሉዓላዊነት መገለጫ ነው። ይህም በሁላችን፣ ከሁላችን፣ ለሁላችን ብልፅግናን የምናረጋግጥበት ምልክታችን ነው።
ስለሆነም፣ ብልፅግና ቃሉን ይጠብቃል፤ ቃሉን ይፈጽማል፤ ሕዝቡን የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ያደርጋል!
እስከ ዛሬ ላስመዘገብነው ውጤት ከጎናችን ያልተለያችሁን ፤ የደገፋችሁን እንዲሁም ዛሬ ማልዳችሁ በታላቅ ሞራል ወጥታችሁ ድጋፋችሁን የገለፃችሁልን ውድ የከተማችን ነዋሪዎች ፈጣሪ ያክብርልን ፥ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
ዳግም ብትመርጡን ከዚህ በላይ በትጋት፣ በታማኝነት እና በቅንነት ልናገለግላችሁ ቃል እንገባለን።